ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስና የፕሮቴስታንት መሪዎች የተመሳሳይ ጾታን የሚያወግዙ አገራትን አወገዙ
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ ከእንግሊዝና ስኮትላንድ አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛ የፕሮቴስታንት እምነት መሪዎች ጋር በመሆን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ወንጀል የሚያደርጉ ሕጎችንና አገራትን አውግዘዋል።
ደቡብ ሱዳን ጉብኝት ላይ የነበሩት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የጉብኝት ማሳረጊያቸው ላይ ለጋዜጠኞች እንዳሉት ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን የሚያወግዙ ሕጎችና ሰዎች ‘ሃጥዕ ናቸው”፤ “ፍርደ ገምድልም” ናቸው ብለዋል።
ጨምረውም፤ የተመሳሳይ ጾታ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች “እነርሱም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያንም እጇን ዘርግታ ልትቀበላቸው ይገባል” ብለዋል።
የሊቀ ጳጳሱ አስተያየት በእንግሊዝና እና በስኮትላንድ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ዘንድ ድጋፍ አግኝቷል።
የስኮትላንድ አንግሊካን አብያተ ክርስቲያናት መሪ ዶ/ር ግሪንሺልድስ እና የእንግሊዝ አብያተ ክርስቲያነት ሊቀጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን አጅበው ነው ወደ ደቡብ ሱዳን ያቀኑት።
የካቶሊክ የአንግሊካንና የፕሮቴስታንት ከፍተኛ መንፈሳዊ መሪዎች በዚህ መንገድ የጋራ ጉብኝት ሲያደርጉ በ500 ዓመት በኋላ የመጀመርያ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።
ሊቀጳጳስ ዌልቢ እና ዶ/ር ግሪንሺልድስ የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በተመሳሳይ ጾታ ወዳጆች ላይ የተጫኑ ሕጎች ዙርያ የሰጡትን አስተያየት በጽኑ እንደሚደግፉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ባለፈው ወር የእንግሊዝ ቤተክርሰቲያን ተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በአብያተ ክርስቲያኖቼ አልባርክም ብላ ነበር።
የአብያተ ክርስቲያናቱ መሪ ዶ/ር ግሪፍን ግን መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ “አራቱንም ወንጌል ብንመለከት ጌታ እየሱስ አንድም ቦታ ፍቅርን ላገኘው የሰው ልጅ ሁሉ ሲሰጥ እንጂ ሌላ አላየሁም” ብለዋል። “እኛም እንደ ክርስቲያን ለሰው ልጅ ሁሉ ፍቅርን እንጂ ሌላ አንሰጥም" ሲሉ የተመሳሳይ ጾታ ወዳጆችን ማግለል ተገቢ እንዳልሆነ አስምረውበታል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ከ50 በላይ አገራት የተመሳሳይ ጾታን ወንጀል እንዳደረጉና ከነዚህም 10 የሚሆኑት የሞት ቅጣት እንደሚበይኑ አስታውሰው ይህ ተገቢ አይደለም ሲሉ ኮንነዋል።
የዓለም የሴት ለሴት፣ ወንድ ለወንድ፣ ‘ባይሴክሹዋል’ እና ‘የልውጥ ጾታ’ (ትራንስጀንደር) ማኅበር የሆነው 'ኢልጋ' (ILGA) በበኩሉ 66 የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ወንጀል አድርገዋል ይላል።
“ይህ በፍጹም ትክክል አይደለም፤ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው” ሲሉ በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ።
ጨምረውም፤ “እነሱን ጌታ ይወዳቸዋል፣ ጌታ ይጠብቃቸዋል እነርሱን መኮነን ሃጥያት እንጂ ሌላ አይደለም” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ጉዳይ ላይ ባለፉት ዓመታት የሰጧቸው አስተያየቶች ምዕመኑን የሚያወዛግብበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።
አሁን ባለው የካቶሊክ አስተምሕሮ የተመሳሳይ ጾታ የሚገለጸው “አፈንጋጭ ባሕሪ” በሚል ነው።
ጥብቅ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በዚህ የተመሳሳይ ጾታ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላትን ትክክለኛ አቋም ምን እንደሆነ በውል እንደማይረዱ ይናገራሉ።
ለምሳሌ በፈረንጆቹ በ2013 ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በሊቀ ጳጳስነት እንደተሾሙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የሃጥያት ተግባር መሆኑን ነገር ግን የተመሳሳይ ጾታ ዝንባሌ በሰው ልጅ መኖሩ ሃጥያት አለመሆኑን ጠቁመው ነበር።
ይህን ካሉ ከ5 ዓመት በኋላ አየርላንድን በጎበኙበት ወቅት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ወላጆች ልጆቻቸው ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ስለሆኑ እንዳያገሏቸውና ፍቅር እንሲሰጧቸው አሳስበዋል።
ከዚያ ወዲህ በተመሳሳይ ጾታ ጉዳይ እያሳዩ ያሉት አቋይ የተለሳለሰ ሆኗል።