ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሚኒሶታ 17 ጊዜ በጥይት ተመትተው ከሞት የተረፉት ባልና ሚስት
ቅዳሜ ዕለት በሁለት የሚኒሶታ ሕግ አውጪዎች ላይ በተፈፀመው ጥቃት በ17 ጥይቶች ከተመቱ በኋላ የተረፉት ግለሰብ፣ "በሕይወት መትረፋችን በሚያስደንቅ ሁኔታ እድለኞች ነን" አሉ።
የግዛቱ ሴናተር ጆን ሆፍማን እና ባለቤታቸው ይቬት ቅዳሜ ማለዳ በቤታቸው ውስጥ ሳሉ በጥይት የተደበደቡ ቢሆንም በሕይወት ተርፈዋል።
ከፍተኛ የዲሞክራቲክ ሕግ አውጪ የሆኑት ሜሊሳ ሆርትማን እና ባለቤታቸው ማርክ በጥይት ተመተው ተገድለዋል።
ይቬት ሆፍማን በሰጡት መግለጫ እርሳቸው እና ባለቤታቸው ጆን በሆርቲማንስ ሞት "በጣም አዝነናል" ብለዋል።
ጭንብል አጥልቆ እንደ ፖሊስ በመልበስ ተጎጂዎቹን በሚኒያፖሊስ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ተኩሶ ያቆሰለው ግለሰብ ያመለጠ ቢሆንም አሁንም እየተፈለገ ነው።
የሆፍማን መግለጫ በሚኒሶታ ሴናተር ኤሚ ክሎቡቻር የኢንስታግራም ገጽ ላይ ተጋርቷል።
ሆፍማን "ጆን ከተደረጉለት በርካታ ቀዶ ሕክምናዎች እያገገመ እና በየደቂቃው ካለበት አስጨናቂ ሁኔታ ለመውጣት እየታገለ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
"በዘጠኝ ጥይት ተመትቷል። እኔ በ ስምንት ጥይት ተመትቻለሁ፤ ሁለታችንም በሕይወት መትረፋችን በሚያስደንቅ ሁኔታ እድለኞች ያደርገናል።
"በሜሊሳ እና ማርክ ሞት እጅጉን አዝነናል፤ ተጎድተናል። ስሜታችንን የምንገልጽበት ቃላት የለንም። ለእንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ጥላቻ መቼም ቦታ የለም።"
ፖሊስ ገዳዩ ጥቃቱን ስለፈፀመበት ምክንያት ያለው ነገር የለም።
የሆፍማን የወንድም ልጅ ነኝ በሚል ግለሰብ የፌስቡክ ገጽ ላይ በግድያው ሙከራ ወቅት ይቬት ልጇን ለማትረፍ በሰውነቷ መከላከሏ ተጽፏል።
"የልጇን ሕይወት ለማትረፍ ሰውነቷን እንደ ጋሻ ተጠቅማለች።"
ሚኒሶታ ስታር ትሪቡን እንደዘገበው ሆፕ የተባለች ሴት ልጇ በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሲሆን ስፒና ቢፊዳ የተባለ የህብለሰረሰር ሕመም ተጠቂ ናት።
ይህም ቀደም ሲል አባቷ ወደ ፖለቲካ እንዲገባ እንዳነሳሳው ገልጾ ነበር።
እሁድ ዕለት ፖሊስ ከተጠርጣሪው ጋር ግንኙነት ያለው መኪና ከግድያው ቦታ 80 ኪሜ ርቀት ላይ በሲብሌይ ካውንቲ ማግኘቱን ተናግሯል።
ጥቁር ሴዳን መኪና መገኘቱን ተከትሎ ፖሊስ "ተጠርጣሪው አልተያዘም፣ በሮቻችሁን ዝጉ፤ ተሽከርካሪዎቸን ጠብቁ" የሚል መልዕክት ወደ የአካባቢው ነዋሪዎች ሞባይል ስልክ በመላክ አስጠንቅቋል።
የ57 ዓመቱ ቦይልተር ለብሶት ነበር ተብሎ የሚታመን የካውቦይ ኮፍያ በአቅራቢያው ተገኝቷል።
ፖሊስ እሁድ ዕለት እንዳስታወቀው የቦይልተር ሚስት ከሦስት ዘመዶቿ ጋር ቅዳሜ ዕለት በመኪናዋ ውስጥ በኦናሚያ ከተማ በቁጥጥር ስር ውላለች።
ጄኒ ቦይልተር ተባባሪ በመሆኗ ወደ እስር ቤት ሳትወሰድ መፈታቷን የሜኔሶታ የወንጀል መከላከል ቢሮ ባልደረባ ድሩ ኢቫንስ እሁድ አመሻሽ ላይ ተናግረዋል።
ፖሊስ ፍለጋውን አስፍቶ የቀጠለ ሲሆን ኤፍቢአይ ደግሞ ቦይልተርን በጣም በሚፈለግ ወንጀለኛ ዝርዝር ውስጥ አስፍሮ ያለበትን ለጠቆመ የ50,000 ዶላር ሽልማት ማዘጋጀቱን ገልጿል።
ሁለቱም ጥቃት የደረሰባቸው የሕግ አውጭዎች የሚኒሶታ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ናቸው።
ባለስልጣናት እንደተናገሩት ተጠርጣሪው በተጠቀመበት ሌላ ተሽከርካሪ ውስጥ የሚኒሶታ ዲሞክራቲክ ፖለቲከኞችን ስም የያዘ ዝርዝር አግኝተዋል።
ክሎቡቻር የተባሉት ፖለቲከኛ ለኤንቢሲ ኒውስ "በግልጽ በፖለቲካ ጥላቻ የተነሳሳ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቃቱን "አስፈሪ " መሆኑን እሁድ እለት ለኤቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።