ቼልሲ ከቶተንሃም እና ሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የባለሙያ ግምት

እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባለፈው ሳምንት ሲመለስ ብዙ ያልተጠበቁ ውጤቶች ተመዝግበውበታል።
ሊቨርፑል አቻ ሲለያይ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው በብራይተን በመሸነፍ የውድድር ዓመቱን ጀምሯል።
ማንቸስተር ሲቲ፣ ቶተንሃም እና አርሴናል ደግሞ ሦስት ነጥብ ካሳኩ ቡድኖች መካከል ናቸው።
የሁለተኛው ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ቅዳሜ ይጀምራሉ።
ቼልሲ ከ ቶተንሃም የሚያደርጉት የስታምፎርድ ብሪጅ ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቀው ነው።
የሁለተኛውን ሳምንት ጨዋታዎች በተመለከተ የቢቢሲው ክሪስ ሱቶን እንደሚከተለው ግምቱን አስቀምጧል።
ቅዳሜ
አስቶን ቪላ ከ ኤቨርተን
ይህ ለመገመት ከባድ ጨዋታ ነው።
ኤቨርተኖች ለአዳዲሶቹ ፈራሚዎች ኮኖር ኮዲ እና እና ለአማካዩ አማዱ ኦናና የመሰለፍ እድል መስጠጥ አለባቸው። በቼልሲ ሲሸነፉ የአጥቂ ችግር እንዳለባቸው ታይቷል። ይህ የአጥቂ ችግር ግን ከቅጣት በሚመለሰው ሳሎሞን ራንዶን የሚፈታ አይመስልም።
ቪላ በበርንማውዝ መሸነፉን አልጠበቀኩም ነበር። ከዚህ ሳምንት ጨዋታ ነጥብ ማግኘት አለባቸው።
አሰልጣኝ ስቴቨን ዤራርድ የአጥቂያቸውን ችግር እንዴት ይፈታሉ?
ግምት፡ 1-1

አርሴናል ከ ሌስተር
ዘንድሮ ምንም ተጫዋች ላላስፈረሙት ሌስተሮች ነገሮች በሙሉ ጥሩ አይመስሉም።
ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ቢኖረወቸውም አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ በሁኔታዎች ደስተኛ አይመስሉም። ባለፈው ሳምንትም 2 ለ 0 ከመምራት አቻ ተለያይተዋል።
በተቃራኒው ደግሞ አርሴናል ቤት ነገሮች አልጋ በአልጋ የሆኑ ይመስላል። ደጋፊዎች ቡድናቸው ዘንድሮ ሊያስመዘግብ በሚችለው ውጤት ከወዲሁ አዎንታዎ ተስፋን ሰንቀዋል።
ጋብርኤል ጄሱስ ለአጥቂ መስመሩ ጥሩ መሻሻል አስገኝቷል። ይህንን ጨዋታ ያሸንፋሉ ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 2 - 1

ብራይተን ከ ኒውካስል
ብራይተን በመክፈቻው ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድን ማሸነፍ ችሏል።
ይህም ለመገመት ከባድ ከሆኑት ጨዋታዎች አንዱ ነው።
ብራይተኖች በአሰልጣኝ ግርሃም ፖተር ስር ጥሩ ቡድን መሆን ችለዋል።
ኒውካስል የመክፈቻውን ጨዋታ ከፎረስት ጋር ነበር ያደረገው። ይበልጥ ወደ ፊት በመሄድ ለመጫወትም ሞክረዋል።
የኤዲ ሆዊ ን ቡድን ማየት ያስደስተኛል። ጨዋታው ጥሩ እንደሚሆን እግመታለሁ።
ግምት፡ 1 - 1

ማንቸስተር ሲቲ ከበርንማውዝ
ኤርሊንገግ ሃላንድ ይህንን ጨዋታ በጉጉት እየጠበቀው እንደሆነ ይሰማኛል። ማንቸስተር ሲቲ ቀድሞ ካገባ ብርማውዝ በጣም ከባድ ይሆንበታል።
በርንማውዞች መከላከል ላይ መሰረት አድርገው ከተጫወቱ የሚሳካላቸው አይመስለኝም።
በርንማውዝ ረዣዥም ተጫዋቾችን የያዘ የሊጉ ቡድን ነው። በዚህ ሳምንት ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል።
ግምት፡ 6 - 0

ሳውዝሃምፐተን ከ ሊድስ
ሊድስ ዎልቭስን በማሸነፍ ጥሩ ጅማሮ አድርጓል። ከሊጉ እንደሚወርዱ ከገመትኳቸው ቡድኖች አንዱ ሊድስ ነው።
ሳውዝሃምፕተኖች ባለፈው ሳምንት መምራት ቢችሉም በቶተንሃም ተደቁሰዋል።
ይህ ሽንፈት የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለማወቅ ከባድ ነው።
ከመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች ስምንት ነጥብ ያገኙ ቡድኖች በሊጉ የመቆየት ዕድላቸው 96 በመቶ ነው።
ስለዚህ ሊድስ እንደሚወርድ ስለገመትኩኝ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ የለበትም።
እንዴት እንደሚያሳካው ባላውቅም ይህንን ጨዋታ ሳውዝሃምፐተን ያሸንፋል።
ግምት፡ 2 – 1

ዎልቭስ ከ ፉልሃም
ዎልቭስ አጥቂ ይፈልጋል። በዚህ ሳምንት ደግሞ ጎንካሎ ጉኤድዝን ማስፈርም ችለዋል።
ድንቅ ብቃት አላቸው ተጫዋቾች ቢኖሯቸውም ከሊድስ ጋር በነበራቸው ጨዋታ እንዳየነው ብቃታቸው ያሳስበኛል።
ሊጉ እስኪረጋጋ ድረስ ከቡርኖ ላዥ ቡድን ምን እንደሚጠበቅ መገመት ከባድ ነው። ከሊቨርፑል ጋር አቻ ከተለያየው ፉልሃም ጠንካር ፉክክር እንደሚጠብቃቸው እገምታለሁ።
ከጨዋታው የፉልሃም ተጫዋቾች ብዙ ጠንካራ ነገሮችን አግኝተዋል። አሌክሳንደር ሚትሮቪች መኖሩ ደግሞ ጎል የማግኘት ዕድላቸውን ያሳድገዋል።
ጨዋታውን ፉልሃም ያሸንፋል ብዬ ባስብም ከሊጉ ይወርዳሉ ብዬ ከምገምታቸው ቡድኖች አንዱ ነው። በዚህ ምክንያት ጨዋታው አቻ ይጠናቀቃል እላለሁ።
ግምት፡ 1- 1

ብሬንትፎርድ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
እንደሌላ ጊዜ ቢሆን በብራይተን ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ማንቸስተር ዩናይትድ ምላሽ እንደሚሰጥ እገምታለሁ።
አሁን ግን አይመስልኝም። ምክንያቱም ቡድኑ ብዙ ቀዳዳዎች አሉት። ኤሪክ ቴን ሃግን ለዚህ ተጠያቂ ባላደርግም ማስተካከል ግን ይጠበቅበታል።
ተከላካይ ስፍራ ላይ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እና ሃሪ ማጓየር ከኢቫን ቶኒ ጋር ጥሩ ይፎካከራሉ ብዬ አልጠብቅም። ሮናልዶ ደግሞ ፊት መስመሩን መምራት አለበት።
እንደ ብራይት ሁሉ ብሬንትፎርድም በደንብ የተደራጀ ቡድን ነው። ማንቸስተር ጥሩ ካልሆነ ውጤታማ የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ነው።
አንዳንዶች ይህንን ግምቴን መጥፎ ሊሉት ይችላሉ። ዩናይትድ ከአጥቂው አርናውቶቪች ጋር ስሙ ከመያያዙ አንጻር መትፎ የሚባል አይደለም።
ግምት፡ 3 - 0
እሑድ
ኖቲንግሃም ፎረስ ከ ዌስት ሃም
ይህ ጨዋታ ለዌስት ሃም ቀላል አይሆንም። ፎረስት ወደ ሊጉ ከተመለሰ በኋላ በሜዳው የሚያደርገው የመጀመሪያው ጨዋታ በመሆኑ ከባድ ይሆንበታል።
ዌስት ሃሞች የተከላካይ መስመራቸውን በጉዳት ሳስቷል። ይሁን እንጂ ድሉ የዌስት ሃም ነው።
ግምት፡ 1- 2

ቼልሲ ከ ቶተንሃም
ቼልሲ ከቶተንሃም ጋር መጫወት ይመቸዋል። ባለፈው ዓመት ብቻ አራት ጊዜ አሸንፈዋቸዋል። ከ1990 ወዲህ ደግሞ በሊጉ ቶተንሃም ቼልሲን በስታምፎርድ ብሪጅ ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ሽንፈቱ ሲያጋጥም ቼልሲን ይመሩ የነበሩት የአሁኑ የቶተንሃም አለቃ አንቶንዮ ኮንቴ ናቸው። በዚህ ጨዋታ ኮንቴ እንደሚቀናቸው አስባለሁ።
ቼልሲ አመርቂ ባይሆንም ኤቨርተንን በማሸነፍ ጥሩ ውጤት አስመዝገቧል።
ቶተንሃሞች ደግሞ ከሳውዝሃምፕተን ጋር በነበራቸው ጨዋታ አጥቂ ስፍራቸው አስፈሪ ሆኖ አምሽቷል። በዚህ ሳምንትም ተመሳሳይ መልክ ይዘው እንደሚቀርቡ እገምታለሁ።
ኮንቴ ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ መመለሳቸውን ሳስብ ደግሞ ቶተንሃም ነጥቡን እንደሚሰበስብ ያለኝን ግምት ያሳድገዋል።
ግምት፡ 1- 2
ሰኞ
ሊቨርፑል ከ ክሪስታል ፓላስ
ፓላስ በአርሴናል ሽንፈትን አስተናግዶ ነው የውድድር ዓመቱን የጀመረው። በዚህ ሳምንትም ነገሮች ቀላል አይሆኑላቸውም።
ባለፈው ሳምንት ከፉልሃም ጋር ነጥብ መጣላቸውን በማሰብ ሊቨርፑሎች በዚህ ጨዋታም ነጥብ ይጥላሉ ተብሎ አይጠበቅም።
ቀያዮቹ የጉዳት ችግር ቢኖርባቸውም ክሎፕ አጥቂያቸው ዳርዊን ኑኔዝን ማስጀመር አለባቸው።
ይህ ጨዋታ ሊቨርፑል ሦስት ነጥብ የሚያገኝበት ሲሆን ለፓላስ ተራራ የመውጣት ያህል ይከብደዋል።
ግምት፡ 4 - 0












