በአፋር ክልል ተይዘው ያሉ ዘጠኝ ሺህ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጆች እንዲለቀቁ ኢሰመኮ ጠየቀ

በማቆያው ውስጥ የሚገኙ ሴት አዛውንቶች

የፎቶው ባለመብት, AM

ታትሟል

በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተይዘው ያሉ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች በአፋጣኝና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ።

ኢሰመኮ በሰመራ ከተማ ሰመራና አጋቲና ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙ መሆናቸውን ጠቅሶ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ ህገወጥ እና የዘፈቀደ እስር መሆኑንም በትናንትናው ዕለት ሰኔ 22፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

ከርስ በርስ ጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑ ሶስት የአፋር ክልል ወረዳዎች በሚገኙ መኖሪያ ቤታቸው የተወሰዱ ወደ 9 ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች በሁለቱ ካምፖች ውስጥ ለወራት ያህል መቆየታቸውን ገልጿል።

በኅዳር ወር በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የትግራይ እና የአፋር የድንበር ከተማ ከሆነችው አብአላ ታፍሰው ወደ ሰመራ መወሰዳቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ገልጸዋል።

 ኢሰመኮ በስፍራዎቹ ተገኝቶ ባደረገው ጉብኝት 8 ሺህ 560 ሰዎች መኖራቸውንና የአንድ ቤተሰብ አባላትም ተለያይተው ለመኖር የተገደዱበትን ሁኔታ ቃኝቷል። ለዚህም ወንዶች እና ሴቶች ተለያይተው የተያዙ በመሆናቸው እንደሆነም ተገልጿል።

እርዳታም ሆነ የህክምና አገልግሎት አቅርቦት እጅግ ውስን መሆኑን የገለጸው የኢሰመኮ ሪፖርት በዚህም የተነሳ በካምፖቹ ወረርሽኝ መሰል በሽታ ህይወት መቅጠፉን ገልጿል። ሪፖርቱ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ አይገልፅም።

ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በሰመራ ካምፕ ብቻ በበሽታ የሞቱ፣ እንዲሁም በወሊድ ወቅት ልጅ የሞተባት እናት መኖራቸውን ኢሰመኮ በካምፑ ባደረገው ጉብኝት ከተያዙ ሰዎች መረዳቱን አስፍሯል።

በተጨማሪም ቤተሰቦቿ የአዕምሮ መረበሽ እክል አለባት በሚል በሰንሰለት የታሰረች ወጣት ሴት፣ እስከ 10 የሚደርሱ ከባድ ቁስል ያለባቸው ግለሰቦች፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው አምስት ህፃናት እንዲሁም የቆዳ በሽታ ወረርሽኝ ተጠቁ የተባሉ ከ4-5 አመት ዕድሜ መካከል የሚገኙ ህፃናት መኖራቸው ተጠቅሷል። 

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግለሰቦቹ በአካባቢው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሄደው ለመታከምም ባለመፈቀዱ የበለጠ ችግሩን አክፍቶታል ብሏል። ወደ ጤና ተቋማቱ ለመሄድ የሚፈቀደው በወሊድ ምክንያት ብቻ መሆኑንም አስፍሯል።

በተለይም የቆዳ ወረርሽኝ በተባለው በሽታ መዛመት የበርካቶቹን ደህንነትና ህይወት አደጋ ላይ እንደጣለውና ህክምናም አለማግኘታቸውን የታገቱት ነዋሪዎች ለኢሰመኮ አስረድተዋል።

የትግራይ ኃይሎች ቅዳሜ ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም. አብአላ ከተማ ገብተው ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ በማግስቱ መውጣታቸውን ቢቢሲ ያናገረው  አብዋሎም የተባለ ግለሰብ የገለጸ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በአፋር የፀጥታ አካላት ከባድ ጥቃት ፈፅመዋል ብሏል።

በዚህም የትግራይ ተወላጆች የሆነ ንብረት፣ ቤት ላይ ተነጥሎ ጥቃት መድረሱን የሚናገረው አብዋሎም፣ “በርካቶች ተገድለዋል፤ ሬሳቸው በየመንገዱ ተጥሎ ሰንብቷል” ይላል።

በሰመራ ማቆያ ስፍራ ውስጥ የሚገኘውና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ወልዳይ ገብረጻዲቅ* በበኩሉ አብዛኛዎቹ በመጠለያው የሚገኙ ሰዎች አርሶ አደሮች እና ነጋዴዎች እንዲሁም የቀን ሠራተኞች መሆናቸውን ተናግሯል። 

በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ለደህንነታቸው ጥበቃ እና በወንጀል ጥርጣሬ የሚፈለጉ ሰዎችን ለመለየት በሚል ምክንያት ከትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑ ሶስት የአፋር ክልል ወረዳዎች ከአብዓለ፣ ከኮነባ እና ከበረሃሌ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ተይዘው መቆየታቸውን ሪፖርቱ አስፍሯል።

የአፋር ክልል የጸጥታ ኃይሎች በዞንና ወረዳ ደረጃ ካሉ ሲቪል አመራሮች ጋር በመሆን ወስደውታል በተባለው እርምጃ የትግራይ ተወላጆችን ለይተው በመሰብሰብ ከታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በመኪና በማጓጓዝ ወደ ካምፖቹ እንዲመጡ ተደርገዋል።

ግለሰቦቹ ከመኖሪያ ቤታቸው ያለፈቃዳቸው እንዲወሰዱ እንደተደረጉና በካምፖቹ ለመቆየት እንደተገደዱ ተናግረዋል።

“በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሰመራና አጋቲና ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙት ሰዎች ሁኔታ በመጠለያ ጣቢያ ስም የተፈጸመ፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እስር በመሆኑ በአፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል፤ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸውም እስኪመለሱ ድረስ በካምፑ ውስጥ ለመቆየት የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩ በሙሉ ፈቃደኝነትና ያለ ማናቸውም ዓይነት የእንቅስቃሴ ገደብ ሊሆን ይገባል” በማለት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መናገራቸውም ሰፍሯል።

ወደ መኖሪያ ስፍራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ወይንም በዚህ ስፍራም ለመቆየት የሚፈልጉ ነዋሪዎች ካሉ አስፈላጊው ድጋፍና እርዳታ ሊደረግላቸውም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥቷል።

“በምክንያታዊ ሁኔታ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ካሉ በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ከሚታይ እና በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ ከሚፈጸም በስተቀር፤ የአሁኑ አያያዝ የሕግ መሰረት የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ በካምፑ የሚገኙትን ሰዎች ለተደራረበ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያጋለጠ በመሆኑ በአፋጣኝና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊያበቃ ይገባል” በማለት ኮሚሽነሩ ማሳሰባቸው ሰፍሯል።