ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጣሊያን ጀልባዎች ላይ የሚገኙ 1 ሺህ 200 ስደተኞችን ለመታደግ ዘመቻ እያካሄደች ነው
የጣሊያን የባህር ዘቦች በሲሲሊ የባህር ዳርቻ በተጨናነቀ ሁኔታ በአንድ ጀልባዎች ላይ በተጨናነቀ ሁኔታ የሚገኙ ወደ 1 ሺህ 200 የሚጠጉ ስደተኞችን ለመታደግ ሁለት መጠነ ሰፊ ዘመቻዎችን እያከናወኑ ነው።
አንድ የአሳ ማጥመጃ ጀልባ 800 ስደተኞችን የጫነ ሲሆን ሌላኛው ጀልባ 400ዎቹን ይዟል።
የሀገሪቱ የባህር ዘብ ካባለፈው አርብ ጀምሮ 2 ሺህ ስደተኞችን መታደግ ችሏል።
ባለፉት የዕረፍት ቀናት በጀልባ ለማቋረጥ ሲሞክሩ የነበሩ ሰዎች መሞታቸውን ለትርፍ ያልተቋቋመ አንድ የጀርመን ተቋም ገልጿል።
በጣሊያን የቀኝ ዘመሙ ጥምር መንግስት መደበኛ ያልሆነ ስደትን ለመግታት እያደረገ ካለው ጥረት በተቃራኒ ጣሊያን የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጨምሯል።
400 ሰዎችን የያዘውና ከሊቢያ ቶብሩክ ግዛት እንደተነሳ የሚታመነው ጀልባ እስከ ሰኞ ማምሻ ድረስ እርዳታ እንደልተደረገለት ለስደተኞች ከተዘረጋ ይፋዊ ካልሆነ የአደጋ ጊዜ የስልክ መስመር የሚያስተዳድረው አላርም ፎን የተሰኘው ተቋም ገልጿል።
በባህሩ ላይ ከነበሩት የማልታ የንግድ መርከቦች አንደኛው ጀልባዎቹ በማልታ የውሃ ክልል በነበሩበት ጊዜ የነፍስ ማዳን ስራ እንዳይደግፍ መታዘዙን ሲ ዋች የተባለው የጀርመን አለም አቀፍ ድርጀት ገልጿል።
ሌላኛው መርከብ ግን ውሃና ነዳጅ እንዲያቀርብ ተፈቅዶለታል። በጉዳዩ ላይ የማልታ መንግሥት ያለው ነገር የለም።
አላርም ፎን እንደገለጸው በጀልባው ላይ ያሉ ሰዎችን እያነጋገረ እንደሆነ ገልጿል። በጀልባው ላይ ያለች አንዲት ሴት በርካታ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጻለች።
800 ሰዎችን የያዘን ሌላኛውን ጀልባ ለመታደግ የሚደረገው ዘመቻ የቀጠለ ቢሆነም ጀልባው ከመጠን በላይ በመጨናነቁ ስራዎችን አስቸጋሪ እንደደረው የጣሊያን ባህር ዘብ ገልጿል።
ጀልባዋ መነሻ እስካሁን አልታወቀም።
ባለፉት የእረፍት ቀናት ሌሎች ጀልባዎች የጣሊያኗ ደሴት በሆነችው ላምፔዱሳ የደረሱ ሲሆን ላምፔዱሳ ወደ አወሮፓ መሻገር የሚፈልጉ ሰዎች መሸጋገሪያ ዋነኛ ወደብ ናት።
ሌላ ጀልባ መስመጡን ተከትሎ ቢያንስ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እና 20 ሰዎች የገቡበት እንደማይታወቅ ተዘግቧል።
እንደ አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት መረጃ ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ከ26 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን ሞተዋል ወይም የገቡበት አልታወቀም።