በሰሜን ለንደን ደርቢ አርሰናል የበላይነቱን በማሳየት ታላቅ ድል አሳካ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እሑድ በተካሄደው የእንግሊዝ ፕሪሜየር ሊግ ጨዋታ የሰሜን ለንደን ተቀናቃኞቹ ቶተንሃም እና አርሰናል ተገናኝነተው መድፈኞቹ ድል ቀንቷቸዋል።

በ64ኛው ደቂቃ የመሃል ተለከላካዩ ጋብርኤል ከማዕዘን የተሻማለትን ኳስ በጭንቅላት አስቆጥሮ የሚኬል አርቴታ ቡደን መሪ እንዲሆን አሰችሏል። ጨዋታው በዚህ ብቸኛ ጎል የተጠናቀቀ ሲሆን አርሰናል ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን ይዞ ተመልሷል።

በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች አርሰናል ሰፐርስን አሸንፎ በደርቢው ያለውን የበላይንት አሳይቷል።

ስፐርሶች ጎሎችን በቀላሉ ለማስቆጠር የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች ቢፈጥሩም አንዱንም ወደ ጎልነት መቀየር አልቻሉም።

የአርሰናል አምበል ማርቲን ኦዴጋርድ በጉዳት እና ዴክለን ራይስ በቀይ ካርድ ምክንያት የሌሉበት ጨዋታ ለቶተንሃም የተመቸ ይሆናል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም ውጤቱ ተቀራኒ ሆኗል።

በተለይ ጋብርኤል ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ስፐርሶች የሚያገኟቸውን ዕድሎች ወደ ጎልነት በመቀየር በኩል ደካማ ውሳኔዎችን ሲወስኑ በተደጋጋሚ ተስተውለዋል።

ደካማ ሆኖ የታየው የስፐርሶች አቀራረብ ደጋፊዎቹን ቅር ያሰኘ ሆኗል። ስፐርሶች ከዚህም ጨዋታ በፊት በሊጉ የነበራቸው አቋም ዝቅ ያለ ነበር። ካለፉት 11 ጨዋታዎች በሰባቱ ተሸንፈዋል።

በተጻራሪው ለደርቢ ጨዋታ ባልተለመደ መልኩ በሶስተኛ ማሊያ የገቡት አርሰናሎች መረባቸውን ላለማስደፈር ሲዋደቁ ታይተዋል። ከተከላካዮቹ እስከ ግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያ የተጋጣሚያቸውን የጎል ዕድሎች በተደጋጋሚ አምክነዋል።

አርሰናል ባለፉት ጨዋታዎች ስፐርስ ላይ ያስቆጠራቸው አራት ጎሎች ከቆሙ ኳሶች የተቆጠሩ ሲሆን ይህም የቶተንሃምን የቆሙ ኳሶች የመከላከል ድክመት ያጋለጠ ሆኗል።

በዚህም ምክንያት የፍጹም ቅጣት ምቶች ሳይካተቱ በወራጅ ቀጣና ከነበሩት ኖቲንግሃም ፎረስት፣ ሉተን ታውን እና ሼፊልድ ዩናይትድ ቀጥሎ ቶተንሃም ከፍተኛ ግብ ያስተናገደ ሆኗል።

ይህም ስፐርሶች ካለፉት ስህተቶቻቸው አልተማሩም የሚል ትችት እንዲሰነዘርባቸው አድርጓል።

ቶተንሃም ከቆሙ ኳሶች ከፍተኛ ጎሎችን በማስተናገድ አራተኛ በሆነበት ተመሳሳይ ጊዜ አርሰናል ደግሞ ፍጹም ቅጣት ምቶች ሳይቆጠሩ ከቆሙ ኳሶች ከፍተኛ ጎል ያስቆጠረ ቡደን ሆኗል።

የሆነው ሆኖ መድፈኞቹ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረውን ጨዋታ በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን ማግኘት ችለዋል።

በዚህም በታሪካዊ ተቃናቃኛቸው ሜዳ ደስታቸውን ከደጋፊዎቻቸው ጋር አጣጥመው ወጥተዋል።