ኢራን የዩክሬንን አውሮፕላን በሚሳኤል መትታ በመጣል በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክስ ቀረበባት

ታትሟል

ኢራን ከሦስት ዓመታት በፊት የዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን የበረራ ቁጥር ፒኤስ752 አውሮፕላን በሚሳኤል መትታ በመጣል በዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት ክስ ቀረበባት።

ክሱን ያቀረቡት አራቱ አገራት ካናዳ፣ ስዊድን፣ ዩክሬን እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው።

አገራቱ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ለነበሩ እና ሕይወታቸውን ላጡ 176 ዜጎቻቸውም ፍትሕ እና ካሳ እየጠየቁ ይገኛሉ።

አውሮፕላኑ ከኢራን መዲና ቴህራን ከተነሳ በኋላ በአገሪቷ የአብዮታዊ ዘብ የአየር መከላከያ ክፍል በተተኮሰ ሁለት ሚሳኤሎች ተመትቶ ወደቀ።

ከሦስት ቀናት በኋላም ኢራን አውሮፕላኑን በስህተት በሚሳኤል መትታ መጣሏን አምናለች።

የአብዮታዊ ዘቡ ኤሮስፔስ ኃይል የአየር መከላከያ ክፍል ቦይንግ 737-800 የሆነውን የዩክሬን አውሮፕላን የአሜሪካን ሚሳኤል ተመሳስሎበት እንደመታው አስታውቋል።

በሚያዝያ ወር የኢራን ፍርድ ቤት 10 ወታደሮች ላይ የእስር ብያኔ ቢያስተላልፍም፣ የተጎጂ ቤተሰቦች ፍርዱን “ትርጉም የለሽ እና ተቀባይነት የሌለው” ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

በአደጋው ዜጎቻቸው የተገደሉባቸው አገራት ኢራን አውሮፕላኑን በሚሳኤል መትታ በመጣል በሲቪል አቪዬሽን ኮንሼንሽን የተደነገጉ ግዴታዎችን ጥሳለች ሲሉም ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ማመልከቻ ላይ አስፍረዋል።

አውሮፕላኑ በሚሳኤል ተመትቶ እንዳይጣል ኢራን አስፈላጊ የሚባሉ እርምጃዎችን አልወሰደችም ሲሉም ከሰዋታል። ይህ አውሮፕላን ተመትቶ የወደቀው በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው።

ይህንንም ተከትሎ ኢራን ገለለልተኛ፣ ግልጽ እና ፍትሃዊ የወንጀል ምርመራ እንዲሁም ክስ መመሥረት ተስኗታል ሲልም የአገራቱ ጥምረት ቡድን ገልጿል።

አገራቱ ኢራን “ዓለም አቀፍ በደል የሆነውን ድርጊቷን በይፋ አምና እንድትቀበል፤ የተጎጂ ቤተሰቦችን ይቅርታ እንድትጠይቅ እና ይህ ዳግም እንደማይከሰት ማረጋገጫ እንድትሰጥ” ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ይፈልጋሉ።

አራቱ አገራት ያቀረቡት ማመልከቻ በተጨማሪም ኢራን የሟቾችን ንብረቶች እንድትመልስ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች ሙሉ እና ለደረሰው ጉዳት ሙሉ ካሳ እንድትሰጥ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።