ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ ከማዕድን ማውጫ ያፈተለከ ነው በተባለ ጋዝ 16 ሰዎች ሞቱ
በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የማዕድን ማውጫ ባፈተለከ ናይትሬት ኦክሳይድ በተሰኘ ጋዝ ምክንያት 16 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ገለጡ።
ከሟቾቹ መካከል ሴቶች እና ሕፃናት ይገኙበታል።
በምሥራቅ ጆሃንስበርግ በምትገኘው ቦክስበርግ አካባቢ የሚገኙ አነስተኛ ኑሮ የሚገፉ ነዋሪዎች ናቸው የጋዝ ልቀቱ ሰለባ የሆኑት።
ረቡዕ ዕለት ያፈተለከው መርዛም ጋዝ በአካባቢው ከሚደረገው ሕገ-ወጥ የወርቅ ቁፋሮ ጋር ሳይገናኝ አይቀርም።
ናይትሬት ኦክሳይድ የተባለው ጋዝ ብዙዉን ጊዜ በወርቅ አውጪዎች ጥቅም ላይ ይውላል።
በአካባቢው ዛማ ዛማስ የተሰኘ ስም የተሰጠው ጋዝ ሥራ ካቆሙ የማዕድን ማውጫዎች የሚሰረቅ ነው።
ከጋዝ ሲሊንደሮቹ አንዱ እጅግ በተጨናነቀው የቦክሰበርግ አውራጃ አንጀሎ አቅራቢያ ተጥሎ ተገኝቷል።
ከዚህ ሲሊንደር መቶ ሜትር ርቀት አቅራቢያ ነው የልቀቱ ሰለባ የሆኑት ሰዎች የተገኙት።
ማንም ወደ ሆስፒታል አልተወሰደም ሲሉ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሥፍራው ሌሎች ሰዎች በጋዝ ልቀቱ ሳቢያ አደጋ ደርሶባቸው እንደሆን ለማጣራት ሥራቸውን ቀጥለዋል።
እኒህ የአደጋ ጊዜ ሰዎች ለቢቢሲ እንደሚገልጡት ተጨማሪ ሰዎች በጋዝ ልቀቱ ምክንያት ሳይሞቱ አልቀሩም።
በዚሁ ከተማ ባለፈው ዓመት የገና በዓል ዋዜማ ተመሳሳይ አደጋ መድረሱ አይዘነጋም።
ከስድስት ወራት በፊት በደረሰው የጋዝ ልቀት አደጋ 41 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።