ሄዝቦላህ መሪው ሐሳን ናስራላህ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን አረጋገጠ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሌባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ መሪው ሐሳን ናስራላህ የእስራኤል አየር ኃይል ቤይሩት ውስጥ በፈጸመው ጥቃት መገደላቸውን አረጋገጠ።
ሄዝቦላህ የመሪውን መገደል ያረጋገጠው የእስራኤል ጦር ኃይል ናስራላህን መግደሉን ይፋ ካደረገ ከሰዓታት በኋላ ባወጣው መግለጫ ነው።
በኢራን የሚደገፈው እና ባለፉት ቀናት ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ ይዞታዎቹ በእስራኤል የአየር ጥቃት ዒላማ ሆነው ጥቃት ሲፈጸምበት የሰነበተው ሄዝቦላህ መሪው የተገደሉት አርብ ዕለት በተፈጸመ የአየር ጥቃት መሆኑን ገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ባወጣው መግለጫ፣ በተፈጸመው ጥቃት የሄዝቦላህ መሪ እና ሌሎችም ከፍተኛ የቡድኑ አመራሮች በጥቃቱ ተገድለዋል።
የእስራኤል መከላከያ እንዳለው በሄዝቦላህ ዋና መቀመጫን “ዒላማ በተደረጉ ጥቃቶች” መሪው እና ሌሎችም አመራሮች ተገድለዋል።
አካባቢው በቤይሩት የሚገኘው ዳሂህ የተባለ ስፍራ እንደሆነ እና “መኖሪያ አቅራቢያ ያለ የውስጥ ለውስጥ መሿለኪያ” እንደነበር ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናንት ጄኔራል ሄርዚ ሃሌቪ ዛሬ ረፋድ ላይ ሠራዊታቸው ሐሳን ናስራላህን መግደሉን ካሳወቀ በኋላ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት እስራኤል ጠላቶቿን እንደማትለቅ ገልጸዋል።
“መልዕክቱ በጣም ግልጽ ነው፤ የእስራኤልን ዜጎች አደጋ ላይ የጣለ ማንም ቢሆን በሰሜንም ይሁን በደቡብ እንዲሁም ከዚያ ባሻገር እንዴት አድነን እንደምናገኘው እናውቃለን።”
ይህ የጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ አጭር የቪዲዮ መልዕክት በሠራዊቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የወጣው የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህን ሠራዊቱ እንደገደለ መግለጫ ካወጣ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነው።
ሄዝቦላህ የመሪውን መገደል በቴሌግራም ገጹ በኩል ባረጋገጠበት ረዘም ያለ መልዕክቱ “የትግሉ መሪ፣ ክቡርነታቸው፣ ታማኙ አገልጋይ ወደ ፈጣሪያቸው ሄደዋል" በማለት መገደላቸውን አሳውቋል።
ሄዝቦላህ ጨምሮም ከእስራኤል ጋር የሚያካሂደው ፍልሚያ እና “ለጋዛ እና ለፍልስጤማውያን” የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲሁም “ሊባኖስን እና የተከበረውን ሕዝቧን በቆራጥነት መከላከሉን ይቀጥላል” ብሏል።
እስራኤል አርብ እለት በዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ ጥቃቱን የፈጸመችው የሄዝቦላህ አመራሮች ባሉበት አካባቢ እንደሆነ ተገልጿል።
የእስራኤል አየር ኃይል ምሽት ላይ ቤይሩት ውስጥ ከባድ የአየር ጥቃት ሲፈጽም ነበር። ዒላማ ያደረገችውም ሐሳን ናስረላህ እና የሄዝቦላህ ወታደራዊ መሪዎችን እንደነበር ገልጻለች።
ሐሳን ናስረላህ ከአውሮፓውያኑ 1992 ጀምሮ የሄዝቦላህ መሪ ነበሩ። ከኢራን አብዮት ጠባቂ ዘብ ጋር ባላቸው ቅርብ ግንኙነት ይታወቃሉ።
እስራኤል ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራሮችን ከመግደሏ ጋር በተያያዘ ንቅናቄው ላይ ጫና አሳድሯል።
ሄዝቦላህ የበቀል ጥቃት ሊፈጽም ይችላል የሚሉ ስጋቶች ያሉ ሲሆን፣ እስራኤል በቤይሩት ላይ ጥቃት ስትፈጽም ነዋሪዎች ሸሽተው ለመውጣት ተገድደዋል።
ደቡባዊ ሊባኖስን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እየወጡ ነው።
እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ከተገደሉ መካከል የሄዝቦላህ የደቡብ ግንባር ኮማንደር እንደሚገኙበት የእስራኤል ጦር ገልጿል።
ይህ ከመባሉ በፊት አሜሪካ ስለ “ሐሳን ናስረላህ ሁኔታ ምንም ምልክት የለም” ማለቷን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።
አሁንም በእስራኤልና በሄዝቦላ መካከል የተኩስ ልውውጥ ቀጥሏል።
በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል እየተካሄደ ያለው ጥቃት እና ጦርነት የተቀሰቀሰው ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ ዘመቻ በጀመረ በማግስቱ ነው።
እስራኤል በጋዛ ላይ ይምታካሂደውን ጦርነት በይፋ የተቃወመው ሄዝቦላህ ከደቡባዊ ሊባኖስ ይዞታዎቹ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል የሚሳዔል እና የሮኬት ጥቃቶችን በየዕለቱ በሚባል ሁኔታ እየፈጸመ አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።
እስራኤልም በአጸፋው በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ የቡድኑ ይዞታዎች እና ተዋጊዎች ላይ የአየር እና የከባድ መሳሪያ ድብደባ ስትፈጽም ቆይታለች።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ በከረመው የአጸፋ ጥቃት ምክንያት በሊባኖስ እና በእስራኤል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል ተገደዋል።
ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት የሚያቆመው በመጪው መስከረም 26 አንድ ዓመት የሚሞላው እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደው ጥቃት ሲቆም ብቻ ነው ብሎ ነበር።












