አሜሪካ የመጀመሪያውን የአርክቲክ አምባሳደር ልትሾም ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በአርክቲክ አካባቢ የሩሲያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መጨመሩን ተከትሎ አምባሳደር ለመሾም ማቀዷ ተነገረ።
በአርክቲክ የሚሾሙት አምባሳደር የአሜሪካ በሰሜናዊ ዋልታ ያላትን ፖሊሲ የሚያስፈጽሙ እንደሆነ የውጭ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ገልጸዋል።
አርብ ዕለት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ዋና አዛዥ ጄንስ ስቶልተንበርግ ሩሲያ በሰሜናዊ የዋልታ ክልሎች ስለደቀነችው ስጋት አስጠንቅቀዋል።
በተጨማሪም ቻይና ወደ አርክቲክ እያደረገቸው ያለችውን መስፋፋት ስጋት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አዲሱ የአሜሪካ አምባሳደር ከሌሎች ሰባት የአርክቲክ ሀገራት ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ አይስላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን እና ሩሲያ እንዲሁም ከቀደምት ህዝቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ይገናኛሉ ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቬዳንት ፓቴል ተናግረዋል።
በአካባቢው ያለው ሰላም እና መረጋጋት ለአሜሪካ "ወሳኝ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ" እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የአገራቸውን አቋም አስረድተዋል።
አንቶኒ ብሊንከን በቅርቡ አምባሳደሩን የሚሰይሙ ሲሆን ይህም ሹመት በሴኔቱ ይሁንታ ማግኘት ይጠበቅበታል ።
አሜሪካ አምባሳደሯን ለመሾም ያስታወቀችው ሩሲያ በሰሜን ዋልታ አቅራቢያ ያላትን ወታደራዊ አቅም ማጠናከሯን እንዲሁም ቻይና የአርክቲክ የምርምር ጣቢያዎችን እየገነባች መሆኗን ተከትሎ ነው።
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ አርብ ዕለት የካናዳ አርክቲክን የጎበኙ ሲሆን በዚያም ሩስያ በሰሜናዊ ክፍል ያላት አቅም “ለጥምር ኃይሉ ስትራቴጂካዊ ፈተና” መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ጸሃፊው እንደ ችግር ከጠቀሷቸው መካከል “በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ እና የቀድሞ የሶቪየት ዘመን የአርክቲክ የጦር ሰፈሮችን” መክፈት እንዲሁም ከፍተኛውን “ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ እጅግ የላቀ የጦር መሳሪያዎች መሞከሪያ” መጠቀሟን ያጠቃልላል።
በተጨማሪም ስቶልተንበርግ ቻይና ወደ አርክቲክ ለሃብት ፍለጋ የምታደርገውን አሰሳ የሚያሳስባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
"ቤጂንግ እና ሞስኮ በአርክቲክ ውስጥ የሚያደርጉትን ዘመቻ እያጠናከሩ ይገኛሉ” ብለዋል።












