በቱፓክ ሻኩር ግድያ የተጠረጠረ ግለሰብ ከ27 ዓመታት በኋላ ተይዞ ክስ ተመሠረተበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሃያ ሰባት ዓመታት በፊት በታዋቂው የሂፕ ሆፕ ሙዚቀኛ ቱፓክ ሻኩር ላይ ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ ላስ ቬጋስ ፖሊስ አንድ ግለሰብን በቁጥጥር ስር አውሎ ክስ መሠረተ።
በወቅቱ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ቱፓክ ሻኩር እንደ አውሮፓውያኑ 1996 እየተጓዘ ከነበረ መኪና ላይ በተተኮሱ ጥይቶች አራት ጊዜ ተመትቶ ነበር ለሞት የተዳረገው።
ነገር ግን ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በአፍሪካ አሜሪካዊው ታዋቂ ሙዚቀኛ ላይ ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ ማንነት ምስጢር እንደሆነ ቆይቷል።
ነገር ግን አርብ ጠዋት በኔቫዳ ግዛት ላስ ቬጋስ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለው የ60 ዓመቱ የቀድሞ የወሮበላ ቡድን መሪ ዳን ዴቪስ ላይ ከቱፓክ ግድያ ጋር በተያያዘ በአደገኛ መሳሪያ ሰውን የመግደል ክስ ተመሥርቶበታል።
ፖሊስ እንዳለው ግለሰቡ በቱፓክ ላይ አደገኛውን ጥቃት የፈጸመው የወንድሙ ልጅ በአንድ የካዚኖ መቆመሪያ ስፍራ ከቱፓክ ከተጣላ በኋላ ነበር።
ዴቪስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው እዚያው ላስ ቬጋስ ውስጥ ካለ ቤቱ አቅራቢያ ሲሆን፣ በቀናት ውስጥም ፍርድ ቤት እንደሚያርበው አስታውቋል።
ለዓመታት የቱፓክን ግድያ ሲመረምር የቆዩት እና በጡረታ ላይ የሚገኙት የፖሊስ መኮንን ግሬግ ካዲንግ ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተረናገሩት በዴቪስ መያዝ ብዙም አልተደነቁም።
“በግድያው ውስጥ ተሳታፊ የነበሩት ሁሉም ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ሞተዋል። ዴቪስ የመጨረሻው በሕይወት ያለ ተፈላጊ ነው” ብለዋል የቀድሞው የፖሊስ መኮንን።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት እንደተናገረው ዴቪስ፣ ‘ሳውዝ ሳይድ ኮምፕተን ክሪፕስ’ የተባለው የጎዳና ላይ ወሮበላ ቡድን ዋነኛ መሪ እና የቱባክ ሻኩርን “ግድያ ያዘዘ ነው” ብሏል።
ፖሊስ አርብ ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተጠርጣሪው የወንድም ልጅ ከቱፓክ ጋር በካዚኖ ስፍራ መጣላታቸውን እና ያንንም ተከትሎ ቱፓክ በትራፊክ መብራት ላይ ቆሞ ሳለ መስከረም 07/1996 (እአአ) ተተኩሶበት ሆስፒታል ከገባ ከሳምንት በኋላ በመስከረም ወር መጀመሪያ 1996 (እአአ) ነበር ሕይወቱ ያለፈው።
ፖሊስ በወቅቱ የወንጀል ድርጊቱ ከወሮበላ ቡድኖች ጋር የተያያዘ መሆኑን የተረዳ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ ምርመራውን እና ክትትሉን ሲያደርግ ቆይቶ ዴቪስን ለመያዝ መብቃቱን ገልጿል።
ፖሊስ አሁን በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ በቱፓክ ላይ ከከተኮሰበት መኪና ውስጥ እንደነበር መናገሩን በመጥቀስ “የሟች ቤተሰብ ለ27 ዓመታት ፍትሕ ሲጠብቅ ቆይቷል” ብሏል።
ቱፓክ ሻኩር በተገደለበት ጊዜ ገና የ25 ዓመት ወጣት ነበር።
በሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ዘርፍ ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የቱፓክ ሻኩር ግድያ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ መነጋገሪያ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ሞቱን ተከትሎ በርካታ ዘጋቢ ፊልሞች ተሰርተዋል።
የቱፓክ የሙዚቃ ሥራዎች በዓለም ዙሪያ ከ75 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ የተሸጡ ሲሆን፣ በሙዚቃ የደረጃ ሠንጠረዥ ላይም የተለያዩ ሥራዎቹ የቀዳሚነት ደረጃን ለመያዝ ችለው ነበር።
ቱፓክ ከሙዚቃው ባሻገርም በተለያዩ ፊልሞች ላይ በትወና በመሳተፍ ስኬታማ ለመሆን ችሎ ነበር።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ሆሊዉድ ውስጥ ለተመረጡ ዝነኞች በስማቸው ለመታሰቢያነት በሚሰጠው የ“ሆሊዉድ ዎክ ኦፍ ፌም” ላይ ስሙ እንዲሰፍር ተደርጓል።












