አሜሪካ የኢኳዶሩን ፖለቲከኛ ገዳይ ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ አለች

ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ የነበረው ፖለቲከኛ ከመገደሉ ጥቂት ደቂቃ ቀደም ብሎ ንግግር እያደረገ የተነሳው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ የነበረው ፖለቲከኛ ከመገደሉ ጥቂት ደቂቃ ቀደም ብሎ ንግግር እያደረገ የተነሳው ፎቶ
ታትሟል

አሜሪካ በኢኮዶር ምርጫ ፕሬዝዳንታዊ እጩ የነበረውን ፖለቲከኛ ግድያ ያቀነባበረውን “ዋነኛ አካል” በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚረዳ ዝርዝር መረጃ ለሚሰጥ የ5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ማቅረቧን ገልጻለች።

በጸረ ሙስና ዘመቻዎቹ የሚታወቀው ፈረናንዲ ቪላቪሴንሲዮ ባለፈው ነሐሴ በአደባባይ ሰልፍ ላይ ሳለ ነበር የተገደለው።

በወቅቱ የኢኳዶሩ ፕሬዝዳንት ከግድያው ጀርባ የተደራጁ ወንጀለኞች ነበሩ ሲሉ ገልጸው ነበር።

አሜሪካ በተጨማሪም ለግድያው ኃላፊነት የሚወስድ የወሮበላ ቡድንን መሪን ለጠቆማት አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደምትሸልም ገልጻለች።

አሜሪካ የፖለቲከኛውን ገዳይ ለጠቆመ ሽልማት እንደምትሰጥ ይፋ ያደረጉት የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን “አሜሪካ የኢኳዶርን ህዝብ መደገፏንና የዲሞክራሲ ሂደቱን ወንጀል በመፈጸም ለማደናቀፍ የሞከሩቱን ወደ ፍትህ ለመቅረብ የሚደረገውን ጥረት ትደግፋለች” ብለዋል።

የፖለቲከኛውን ገዳይ ለማድረግ የሚደረገው ምርመራ በኤፍ ቢ አይ ድጋፍ እየተደረገለት እንደሆነ የጠቀሱት ብሊንከን የሽልማቱ መቅረብ አሜሪካ የተደራጁ ወንጀለኞችን ለመፋለም ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

በተሰነዘረባቸው ጥቃት የተገደሉት ቪላቪሴንሲዮ የምርጫ ዘመቻቸው በሙስናና በተደረጁ ወንጀለኛ ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ ነበር። በተጨማሪም ፖለቲከኛው በኢኳዶር መንግሥትና በበወሮበላ ቡድኖች መካከል ግንኙነት አለ ብለው ከሚከሱ ጥቂት የምርጫ እጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

በተገደሉበት ጊዜ የምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆኑ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ጋዜጠኛ ሆነው ሰርተዋል።

ፖለቲከኛው ወሮበላ ቡድኖችን ለመቆጣጠር የተሰጠው ትኩረት ያነሰ እንደሆነ በመግለጽ ታቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ሲሆን እሳቸው ስልጣን ከያዙ ይህንን እንደሚዋጉ ይገልጹ ነበር።

ፖለቲከኛው ከመገደላቸው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የኢኳዶሯ ማንታ ከተማ ከንቲባ በተከፈተባቸው ተኩስ ተገድለዋል።

በየካቲት ወር ደግሞ የፔትሮ ሎፔዝ ከተማ ከንቲባ ከተማ ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ ሳለ ተገድለዋል።

ሆኖም በአደባባይ በፕሬዝዳንታዊ እጩ ላይ የተከፈተው ተኩስ ግን እጅግ ድፍረት የተሞላበት አሰቃቂና ወሮበላ ቡድኖች በኢኳዶር ያላቸውን አቅም ያሳየ ነው ተብሏል።

በታሪክ ኢኳዶር በንጽጽር ከሌሎች የላቲን አሜሪካ ሀገሮች የተሻለ ደህንነትና መረጋጋት ሰፍኖባት የቆየች ናት።

ሆኖም ከቅርብ አመታት ወዲህ በኮሎምቢያና ሜክሲኮ እጽ አዘዋዋሪዎች በሀገር ውስጥ ካሉት ጋር ወሮበላ በድኖች ጋር ዘልቆ በመግባታቸው ምክንያት ወንጀሎች አሻቅበዋል።

ከፖለቲከኛው ግድያ ጋር በተያያዘ የኮሎምቢያ ዜግነት ያላቸው ስድስት ሰዎች በፖሊስ የተያዙ ቢሆንም ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እስካሁን ፍለጋው ቀጥሏል።

አሜሪካ በሌሎች ሀገሮች ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን ለጠቆመ ገንዘብ እሰጣለሁ ስትል ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።

በዚህ ሳምንት እንኳን በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን የአልሸባብ ቡድን ምክትል መሪ አቡካር አለ አዳን ለጠቆመ እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር እስሸልማለሁ ብላለች።

ባለፈው ዓመትም የአሜሪካ የጸረ አደንዛዥ ዕጽ መስሪያ ቤት የአየርላንድ ዜግነት ያለን እና የተደራጀ የወንጀል ቡድን ቁልፍ መሪ የሆነውን ኪኒሃንን ለጠቆመ ገንዘብ እንደሚሸልም ይፋ አድርጎ ነበር።