የናይጄሪያ ፖሊስ አዛዥ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አልፈጸሙም በሚል እስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, AFP
የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አላከበሩም የተባሉት የናይጄሪያ ፖሊስ አዛዥ ኡስማን አልካሊ ባባ በአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሦስት ወራት እስር ተፈረደባቸው።
በአዛዡ ላይ ይህ የእስር ውሳኔ የተላለፈው ከ30 ዓመታት በፊት ከፖሊስ አባልነት የተባረረ ግለሰብ ያቀረበውን ክስ ተከትሎ ነው።
ከሳሽ የፖሊስ መኮንኑ በወቅቱ በግድ ጡረታ እንዲወጣ መደረጉን በመቃወም ነበር ክስ ያቀረበው። ውሳኔውም ኋላ ላይ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።
ነገር ግን ግለሰቡ ወደ ሥራው ሳይመለስ በመቆየቱ የናይጄሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፖሊስ ዋና አዛዥ የሆኑት ኡስማን አልካሊ ባባ፣ የፖሊስ መኮንኑን ወደ ሥራው የማይመልሱት ከሆነ ለሦስት ወራት እንዲታሰሩ ውሳኔ አሳልፏል።
አስካሁን ድረስም የናይጄሪያ ፖሊስ ሠራዊት ውሳኔውን ተግባራዊ ባለማድረጉ በቀጣይ ምን ሊከሰት እንደሚችል እየተጠበቀ ነው።
የፍርድ ቤቱው ውሳኔ ተከትሎ የፖሊስ ቃል አቀባይ ኦሉሙይዋ አዴጆቢ፣ የተሰጠውን ፍርድ “አስደናቂ” ብለውታል።
ጨምረውም የናይጄሪያ ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ብይን ተከትሎ ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ለማወቅ ጥናት እያደረገ ነው ብለዋል።
“የፍርድ ቤቱ ብይን የሰጠበት ጉዳይ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በሆነ ጉዳይ ላይ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። በዚያ ወቅት አሁን ቅጣት የተበየነባቸው የፖሊስ አዛዥ የፖሊስ አባል ከሆኑ ጥቂት ዓመት ብቻ ነበር ያስቆጠሩት” በማለት አዛዡ በመሪነት ቦታ ላይ በሌሉበት ጉዳይ እንዲቀጡ መወሰኑ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።
ከአስርት ዓመታት በላይ ሲንከባለል የቆየው የፖሊስ መኮንኑ ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጠበት ከ11 ዓመት በፊት ሲሆን “ጉዳዩ አሁን የፖሊስ አዛዥ የሆኑትን ግለሰብ የሚመለከት አይደለም” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተከራክረዋል።
በፖሊስ አዛዡ ላይ የተላለፈው ውሳኔ በርካታ ናይጄሪያውያንን እያነጋገረ ሲሆን፣ በቀጣይ ምን ሊከሰት እንደሚችል ሁሉም በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
የፖሊስ አዛዡ እስር ሲፈረድባቸው ከናይጄሪያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የመጀመሪያው አይደሉም። ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እና የገንዘብ ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚቆጣጠረው ኮሚሽን ኃላፊ ተመሳሳይ ቅጣት ተበይኗል።
ኮሚሽነሩ አብዱልራሺድ ባዋ ችሎት ተዳፍረዋል በሚል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በእስር እንዲቀጡ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ ነገር ግን በኋላ ላይ ዳኛው ውሳኔያቸውን አንስተዋል።












