በደርሶ መልስ ጨዋታ በራሱ ስህተት 4 ግብ ያስተናገደው ዩናይትድ ከዩሮፓ ሊግ ተሰናበተ

አምበሉ ማጉዋዬር በራsኡ ቡድን ላይ ሁለት ግቦች ለመቆጠራቸው ምክንያት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አምበሉ ማጉዋዬር በራሱ ቡድን ላይ ሁለት ግቦች ለመቆጠራቸው ምክንያት ሆኗል።
ታትሟል

በደርሶ መልስ ጨዋታ በራሱ ተጫዋቾች ስህተት 4 ግብ ያስተናገደው ማንቸስተር ዩናይትድ ከዩሮፓ ሊግ ተሰናበተ።

ማንቸስተር ከዩናይትድ በዩሮፓ ሊግ ከስፔኑ ሴቪያ ጋር በነበረው የሩብ ፍጻሜ የደርሶ መልስ ጨዋታ በአጠቃላይ ውጤት 5ለ2 ተሸንፏል።

ዩናይትድ ከተቆጠሩበት 5 ግቦች ሁለቱ የዩናይትድ ተጫዋቾች እራሳቸው ላይ ያስቆጠሩት ሲሆን ሁለቱ ግቦች ደግሞ በራሱ ተጫዋቾች ስህተት ምክንያት የተቆጠሩበት ናቸው።

ከሳምንት በፊት በነበረው የመጀመሪያው ጨዋታ በዩናይትድ ሜዳ ተደርጎ የነበረ ሲሆን ጨዋታው 2 አቻ መጠናቀቁ ይታወሳል።

በዛ ጨዋታ ዩናይትድ በአማካዩ ሳቢትዘር አማካይነት ሁለት ጎሎችን አከታትሎ አግብቶ 2ለ0 መምራት ችሎ የነበረ ቢሆንም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ማላሲያ እና አምበሉ ሃሪ ማጉዋዬር እራሳቸው ላይ ጎል አስቆጥረው ጨዋታው 2ለ2 ተጠናቆ ነበር።

ትናንት በነበረው ጨዋታም አምበሉ ማጉዋዬር ጨዋታው በተጀመረ በ8ኛው ደቂቃ የሰራውን ስህተት ተከትሎ የሲቪያው ሞሮኳዊ ኤል-ናስሪ ዕድሉን ተጠቅሞ ቡድኑ መሪ ማድረግ ችሏል።

ማጉዋዬር ከግብ ጠባቂው ዴሂያ ያለፈለትን ኳስ መቆጣጠር ሳይችል በመቅረቱ ምክንያት ነው ዩናይትድ ግብ የተቆጠረበት።

በ81ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የዩናይትዱ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴሂያ በሰራው ስህተት ጎል ተቆጥሮበት በአጠቃላይ ውጤት 5-2 በሆነ ውጤት ዩናየትድ ከዩሮፓ ሊግ ተሰናብቷል።

በላ ሊጋው ከወራጅ ቀጠና በስድስት ነጥብ ብቻ ርቆ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሴቪያ በዩሮፓ ሊግ ግን ጠንካራ አቋም እያሳየ ይገኛል። በግማሽ ፈጻሜው ደግሞ ከጣሊያኑን ጁቬንቱስ ጋር ይገኛል።

በሌሎች የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሮማ ፌዬኖርድን 4-2፣ ሊቨርኩሰን ደግሞ ዩኒየን ሴንት-ጊሎይስን 5-2 እንዲሁም ጁቬንቱስ ስፖርቲንግ ሊዝበንን 2-1 በሆነ አጠቃላይ ውጤት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።

በግማሽ ፍጻሜው ሮማ ከ ሊቨርኩሰን የሚገናኙ ሲሆን ጁቬንቱስ ደግሞ ከሲቪያ ደርሶታል። አራቱ ክለቦች ግንቦት መጀመሪያ ላይ የግማሽ ፍጻሜያቸውን ያደርጋሉ።

ከዩሮፓ ሊግ የተሰናበተው ዩናይትድ የፊታችን እሁድ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘውን ብራይተንን በኤፍ ኤ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ይገጥማል። ከአራት ቀናት በኋላ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አራተኛ ለመጨረስ በሚደረገው ትንቅንቅ ቶተነሃምን ለመግጠም ወደ ሰሜን ለንደን ይጓዛል።