ቢዮንሴ እና አቡነ ፍራንሲስ የትዊተር ‘ሰማያዊ ምልክት’ አጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢዮንሴ እና አቡነ ፍራንሲስ ትዊተር ላይ ‘ሰማያዊ ምልክት’ ካጡ ታዋቂ ግለሰቦች መካከል ናቸው።
ትዊተር ከትላንት ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዋቂ ሰዎችን ሰማያዊ ማረጋገጫ ምልክት ማንሳት ጀምሯል።
ግለሰቦቹ ትክክለኛ ገጻቸው እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳው ሰማያዊ ምልክት ለማግኘት በዓመት 84 ዶላር እንደሚያስከፍል ትዊተር መግለጹ አይዘነጋም።
ትዊተር ክፍያው ካልተፈጸመ ሰማያዊ ምልክት እንደሚነሳ አስታውቆ ነበር።
ብዙዎች በነገሩ ሲሳለቁ እንዳንዶች በውሳኔው ሲያዝኑም ነበር።
ጄሰን ሱዴኪስ የተባለው ተዋናይ ሰማያዊ ጭረቱ ቢሰረዝም ወክሎት የሚጫወተው ልቦለዳዊ ገጸ ባህሪ ቴድ ሎሶ እስካሁን ሰማያዊ ጭረቱ አለመነሳቱ አነጋግሯል።
ራፐሩ አይስ ቲ በበኩሉ “ሰማያዊ ጭረት እርባና ቢስ ነው። ማኅበረሰቡ ይሄን ጉዳይ አድርጎ ማውራቱ ያሳዝናል” ብሏል።
የትዊተር ሰማያዊ ጭረት የግለሰቡን ትክክለኛ ማንነት ከማረጋገጥ ባለፈ እንደ ክብርና ሞገስ መቆጠር ጀምሯል።
ትዊተር ለሰማያዊ ምልክት እንደሚያስከፍል ከመግለጹ በፊት ካንዬ ዌስት፣ ሻክ እና ኢዋን መግሬጎር ትዊተር ላይ በስማቸው ገጽ የከፈቱ ሰዎች እንዳሉ ቅሬታ አሰምተዋል።
የታዋቂ ግለሰቦች ሰማያዊ ምልክት የሚነሳ ከሆነ ታዋቂ ሰዎችን በማስመሰል ገጽ በሚያወጡ ሰዎች እና በትክክለኞቹ ታዋቂዎች መካከል ያለው ልዩነት የተከታዮቻቸው ቁጥር ብዛት ሊሆን ይችላል።
ሰማያዊ ጭረት ከተነሳ በኋላ አንድ በሂላሪ ክሊንተን ስም የወጣ ገጽ ላይ “በቀጣዩ ምርጫ እወዳደራለሁ” ተብሎ ተጽፏል።
በኒው ዮርክ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን አስመስሎ የወጣ ገጽም ውዝግብ ፈጥሯል።
እንዲህ ያለ ውዝግብ ለሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እንደሚዳርግ ባለሙያዎች እሰተያየት ሰጥተዋል።
ኤለን መስክ ሰማያዊ ጭረት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይዘት በገጹ እንዲዘዋወር ይረዳል ብሎ ቢከራከርም ተቺዎቹ እንደሚሉት ትዊተር ሰማያዊ ጭረት ለሚሰጣቸው ሰዎች ቅድሚያ እየሰጠ የገጹ ሚዛናዊነት ሊዛባ ይችላል።












