ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመንግሥታቱ ድርጅት ቻይናን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ከሰሰ
የተባበሩት መንግሥታት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ በነበረው ሪፖርቱ ቻይና በሺንጃንግ ግዛት ‘በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን' ፈፅማለች ሲል ከሰሰ።
ቻይና የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርቱን እንዳያወጣ ስታስጠነቅቅ የነበረ ሲሆን፣ ሪፖርቱን “በምዕራባውያኑ ኃያላን የተቀናጀ ድራማ ነው” ብላዋለች።
ሪፖርቱ በዊጋ ሙስሊሞች እና በሌሎች ቁጥራቸው አነስተኛ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ደርሷል ያለውን በደል ተመልክቷል። ቻይና ግን ይህንን ክስ አልተቀበለችውም።
ሆኖም መርማሪዎች ‘በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች’ ሊሆኑ የሚችሉ ማሰቃየት እንደተፈፀመ “ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ” ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ሪፖርቱ ጨምሮም ቻይና አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ማኅበረሰቦች ለመጨቆን እና ‘የዘፈቀደ እስር’ ለመፈፀም የሚያምታቱና ግልጽ ያልሆኑ የብሔራዊ ደኅንነት ሕጎችን ትጠቀማለች ሲል ከሷል።
በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጽ/ቤት አማካኝነት የተሰራው ሪፖርቱ እስረኞች ወሲባዊ እና ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ጨምሮ እንግልት ደርሶባቸዋል ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የግዳጅ ሕክምና እና አግላይ በሆነ ሁኔታ የቤተሰብ ዕቅድ እና የእርግዝና መቆጣጠሪያ ፖሊሲዎች ተፈጻሚ እንደሆኑባቸው ሪፖርቱ አመላክቷል።
በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት “አንዳንድ የቤይጂንግ ድርጊቶች፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ ናቸው” ሲል ቻይና ያለምንም ሕጋዊ መሠረት በዘፈቀደ ያሰረቻቸውን ግለሰቦች በሙሉ እንድትለቅ አሳስቧል።
ተመድ ምን ያህል ሰዎች በቻይና መንግሥት ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ እርግጠኛ መሆን ባይችልም፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ቁጥራቸው ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆን ሰዎች በሰሜን ምዕራብ ቻይና፣ ሺንጃንግ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ካምፖች ታስረው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
60 የሚሆኑ ድርጅቶችን ያቀፈው የዎርልድ ዊጋ ኮንግረስ ሪፖርቱን የተቀበለው መሆኑን ገልጾ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል።
የዊጋ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት ዳይሬክተር ኦመር ካናት “ምንም እንኳን ቻይና የቀረበባትን ክስ ባትቀበለውም ሪፖርቱ በዊጋ ለደረሰው ቀውስ ዓለም አቀፍ ምላሽ ለማግኘት የሚያስችል ነው። አሁን የተባበሩት መንግሥታት አሰቃቂ የሆኑ ወንጀሎች መፈፀማቸውን ተረድቷል” ብለዋል።
በቻይናዋ ሺንጃንግ ግዛት ወደ 12 ሚሊየን የሚጠጉ ዊጋዎች ይኖራሉ። አብዛኞቹ ሙስሊም ናቸው።
በሪፖርቱ ላይ ሙስሊም ያልሆኑ የማኅበረሰቡ አባላትም በተጠቀሱት ወንጀሎች ተጎድተው ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ጠቁሟል።
ቀደም ብሎ በርካታ አገራት ቻይና በሺንጃንግ የፈፀመችውን ድርጊት “ የዘር ማጥፋት” ሲሉ ገልጸውታል።
ሆኖም ቀደም ብሎ ሪፖርቱን የተመለከተችው ቤይጂንግ የቀረበባትን የመብት ጥሰት ክስ ውድቅ ያደረገችው ሲሆን፣ ካምፖቹ ‘ሽብርተኝነትን ለመዋጋት’ እንደምትጠቀምበት ገልጻለች።
በጄኔቫ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የቻይና ተወካይ፣ “የቻይናን ስም ማጠልሸትና በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ መግባት ነው” ሲል የሪፖርቱን ግኝቶች ውድቅ አድርጎታል ።
ልዑኩ ባወጣው ዘለግ ያለ መግለጫ፣ እውነታውን ችላ ያለ እና ‘ምርመራ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ፖለቲካዊ ሰነድ የአሜሪካ ፣ የምዕራባውያን አገሮች እና ፀረ ቻይና ኃይሎች ሰብዓዊ መብቶችን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ለመጠቀም ያላቸውን ፍላጎት ፍንትው አድርጎ ያመላከተ ነው ብሏል።
ሪፖርቱ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሚሸል ባሽሌት ከአራት ዓመታት የሥራ ቆይታ በኋላ በመጨረሻዋ የሥራ ቀናቸው ነበር።
ባሽሌት በኮሚሽኑ በነበራቸው ቆይታ በርካታ በዊጋዎች ላይ የደረሰ የመብት ጥሰት ክስ ቀርበውላቸዋል።
የባሽሌት መሥሪያ ቤት ከአንድ ዓመት በፊት በቻይና በዊጋ ሙስሊሞች ላይ ደርሷል ስለተባለው ‘የዘር ማጥፋት’ ወንጀል ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጾ ነበር።
ይሁን እንጂ እስካሁን ይፋ አልተደረገም ነበር። ይህም አንዳንድ የምዕራባውያን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሪፖርቱ ላይ የተገኙ ማስረጃዎችን ኮሚሽነሯ እንዲያጠፉ ቤይጂንግ ስታስጠነቅቅ ነበር የሚሉ ክሶችን አስከትሏል።
ይህ ሪፖርት ከመውጣቱ የመጨረሻ ሰዓታት በፊት ቻይና ሪፖርቱ እንዳይወጣ በባሽሌት ላይ ጫና አሳድራ እንደነበር ተነግሯል።
ሐሙስ ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባሽሌት “ሪፖርቱን ይፋ ለማድረግ አሊያም ላለማድረግ” ከፍተኛ ጫና እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
በሪፖርቱ ላይ ከቤይጂንግ ጋር መነጋገር ቀላል እንዳልነበር የገለጹት ባሽሌት፣ ሪፖርቱ ዘግይቷል መባሉን አልተቀበሉትም።
የቻይና የሂዩማን ራይትስ ዎች ዳይሬክተር ሶፊ ሪቻርድሰን የሪፖርቱ ውጤቶች “የቻይና መንግሥት ሪፖርቱ እንዳይወጣ ሲከላከል የነበረው ለምን እንደሆነ አሳይተዋል” ብለዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የቻይና መንግሥት የዊጋ ሙስሊሞችንና ሌሎችን ኢላማ በማድረግ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የፈፀመውን ወንጀል ላይ ምርመራ ለማድረግና ተጠያቂ ለማድረግ ይጠቅማል ሲሉም ዳይሬክተሯ አክለዋል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ አንገስ ካላማርድ ሪፖርቱ ዘግይቶ መውጣቱን አውግዘው፣ በመብት ጥሰቱ የተሳተፉ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ቢቢሲ በካምፕ በሚገኙ ዊጋ ሙስሊሞች ላይ የተደራጀ የጅምላ አስገድዶ መድፈር፣ ወሲባዊ ጥቃት እና ማሰቃየት እንደተፈፀመባቸው የሚያመላክት ሾልኮ የወጣ ሪፖርት አግኝቶ ነበር።
ይህ ሾልኮ ወጥቶ ለቢቢሲ የተላለፈው የሺንጃንግ ፖሊስ ሰነድ፣ ከቻይና መሪ ዢ ጂንፒንግ ጀምሮ ባለው የትዕዛዝ ሰንሰለት በማኅበረሰቡ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መድረሱን አመልክቷል።
ከዚህም ባሻገር እንደ አውሮፓውያኑ 2020 የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ፣ ቻይና በሙስሊም ማኅበረሰቡ ላይ “መጠነ ሰፊ እና አስደንጋጭ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅማለች” ሲሉ ከሰዋል።
ዶሚኒክ ይህን ያሉት የዊጋ ሙስሊሞች ዓይናቸው ተሸፍኖ ባቡር ውስጥ እንዲገቡ ሲደረጉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መውጣቱን ተከትሎ ነው።
ምስሉ ዓለም አቀፍ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በዩኬ የቻይና አምባሳደር ሊዩ ሺያሚንግ፣ በሺንጃንግ እንደዚህ ዓይነት ማጎሪያ ካምፖች የሉም ሲሉ ክሱን አጣጥለውታል።