ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "አሜሪካ ጥቁሮች ላይ የምታደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት" እንድታቆም ጠየቁ
ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በተደረገ የቻይና-አሜሪካ የንግድ ምክክር መድረክ በሁለቱ ኃያል አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ውይይት እየተደረገ ሲሆን ጠጣር የሐሳብ ልውውጦች መደረጋቸው ተሰማ፡፡
በዚህ የሁለትዮሽ ስብሰባ አንዱ ሌላውን አገር ያለ ርሕራሔ እየወቀሰ ይገኛል፡፡
የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት አሜሪካን ሌሎች አገሮች ቻይና ላይ ጦር እንዲሰብቁ ታበረታታለች ሲሉ ከሰዋል፡፡
አሜሪካ በበኩሏ ቻይና በዓለም አቀፍ ደረጃ አላስፈላጊ ትኩረትን ለመሳብ ትጥራለች ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል አሁን ያለው ግንኙነት የሻከረ የሚባል እንደሆነ ዲፕሎማቶች ያወሳሉ፡፡
አሜሪካ በዚህ ስብሰባ ላይ አጨቃጫቂ የሚባሉ ጉዳዮችን እንደምታነሳ ይጠበቃል፡፡ ከነዚህ አንዱ ቤጂንግ የኡህጉሩ ሙስሊሞችን በዢንዣንግ ካምፕ ውስጥ የምታደርስባቸውን ስቃይ እንድታቆም ይጠይቃሉ ተብሏል፡፡
ይህ በቃላት ጦርነት የታጀበ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባ እየተካሄደ ያለው በአላስካ ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሰሊቫን ተገኝተውበታል፡፡
በቻይና በኩል ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ባለሥልጣን ያንግ ጂቺ ተሳትፈዋል፡፡
በሁለትዮሹ ስብሰባ በጠንካራ ንግግር ውይይቱን ያስጀመሩት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን አሜሪካ በዚህ ስብሰባ የሚያሳስቧትን የዢንዣንግ ሙስሊሞች አፈና፣ የሆንግ ኮንግን እና የታይዋንን ጉዳይ እንዲሁም ከቻይና የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ጉዳይ ታነሳለች ብለዋል፡፡
ለዚህ ምላሽ የሰጡት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያንግ ዋሺንግተን ባላት የፋይናንስና የወታደራዊ ኃያልነት የተነሳ ሌሎችን ትደፈጥጣለች ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
አክለውም አሜሪካ በብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ስም በርካታ የንግድ ወንጀሎን ትፈጽማለች ብለዋል፡፡ ሌሎች አገራትም ቻይና ጋር ወዳጅ እንዳይሆኑ ታስፈራራለች ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአሜሪካ የሰብአዊ መብት ጥሰት መባባሱን ጠቅሰው ጥቁሮች በጠራራ ፀሐይ እየተገደሉ ነው ሲሉ አስገራሚ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ይህ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ የሚደረገው መተቻቸት የዓለም ሚዲያዎች በተገኙበት እየሆነ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
ይህ አንድ ሁለት መባባል እየተካረረ ከሄደ በኋላ አሜሪካ ቻይናን ‹የተስማማነው 2 ደቂቃ የመክፈቻ ንግግር ለማድረግ ቢሆንም በዚህ ስብሰባ ቻይና መስመር አልፋ ወቅሳኛለች ስትል ከሳታለች፡፡
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደተናገሩት ቻይና በዚህ ስብሰባ ሆን ብላ የዓለም ሚዲያውን ትኩረት ለመሳብ ተዘጋጅታ ነው የመጣችው ብለዋል፡፡
ቻይና በበኩሏ ስብሰባው መክፈቻ ላይ ለ2 ደቂቃዎች ብቻ እንወቃቀስ ብንባባልም ይህን ፕሮቶኮል የጣሰችው አሜሪካ ራሷ እንጂ እኛ ቻይናዊያን አይደለንም ብለዋል፡፡
ጨምረውም አሜሪካ የቻይናን የውጭና የአገር ውስጥ ፖሊሲ በዓለም ሚዲያ ፊት ለማብጠልጠል መሞከራቸው አሳፋሪ ነው ብለዋል፡፡
ሁለቱ አገሮች በዚህ ስብሰባ በትራምፕ ዘመን አፈር ልሶ የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሻሻል እንደሚጥሩ ይጠበቃል፡፡