ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዱባይ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ እሳት ተነስቶ 16 ሰዎች ሞቱ
በዱባይ በጋራ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ በተቀሰቀሰ እሳት 16 ሰዎች መሞታቸውን እና 9 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የእሳት አደጋው የተቀሰቀሰው አል ራስ ተብሎ በሚጠራውና በዱባይ ካሉ ቀደምት አከባቢዎች በአንዱ ሲሆን፤ በርካታ ስደተኛ ሰራተኞችና ነጋዴዎች የሚኖሩበት አካባቢ ነው።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ባለአምስት ወለል ህንጻ ላይ የተቀሰቀሰው እሳት መነሻ አራተኛ ፎቅ ላይ ያጋጠመ እሳት ነው።
የዱባይ የሲቪል ደኅንነት መስሪያ ቤት እሳቱ የተቀሰቀሰው የሕንጻን ደህንንት መስፈርቶች በአግባቡ ስላልተገበሩ ነው ብሏል።
ባለፈው ቅዳሜ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት የእሳት አደጋ ሠራተኞች በፍጥነት በቦታው ተገኝተዋል።
አልራስ በወርቅና ቅመማቅመም ንግድ የሚታወቅ የጎብኚዎች መስህብ የሆነ አካባቢ ነው።
የዱባይ ሲቪል ደህንነት መስሪያ ቤት ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን የእሳት አደጋ መነሻ ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ገልጿል።
ተቋሙ የመኖሪያና የንግድ ሕንጻ በለቤቶችና ነዋሪዎች አደጋዎችን ለመከላከል እና የሰዎችን ሕይወት ለመጠበቅ የደህኅነት መሰፈርቶች ሳይሸራረፉ ሊተገበሩ ይገባል ብሏል።
ከሟቾቹ መካከል አራት ሕንዳውያን እና ሦስት ፓኪስታናውያን እንደሚገኙበት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ከአደጋው ጋር በተያያዘ እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው አለመኖሩም ታውቋል።