ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትንሳኤ እና ተጠቃሽ የሥነ ግጥም ሥራዎች
ከትንሳኤ በፊት ባለው እሁድ ከሚከበረው የሆሳዕና ዕለት ጀምሮ፣ ከትንሳኤ ዕለት እሁድ በኋላ አስካለው ዳግማ ትንሳኤ ዕለት ድረስ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ያለው ጊዜ በፋሲካ በዓል ድባብ የሚደምቁ ሳምንታት ናቸው።
ከበዓሉ ሽርጉድ እና ድባብ በተጨማሪ ወቅቱን የሚዘክሩ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ የኪነጥበብ ሥራዎች ይነሳሉ። ከሥነ ግጥም ዘርፍ ደግሞ ከትንሳኤ ሰሞን ጋር የሚገጥሙ ሥራዎችም ይነሳሉ።
ከእነዚህም መካከል የገጣሚ ኤፍሬም ስዩም “የጅራፍ ንቅሳት”፣ የገጣሚ ደምሰው መርሻ “የክርስቶስ ሐሙስ”፣ የገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ “የይሁዳ ሚስት” በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
በዚህም የተነሳ የእነዚህ ገጣሚያን ሥራዎች ትንሳኤን ለማድመቅ በግጥም ወዳጆች ዘንድ የሚነሱ፣ የሚጠቀሱ ሆነው ከበዓሉ ምንነት እና ድባብ ጋር አብረው ይነሳሉ። ለዚህም የገጣሚያኑ ሥራዎች በዚህ ወቅት መታወሳቸው እና መወሳታቸው ‘የትንሳኤ አድማቂ’ ገጣሚያን ቢባሉ አይበዛባቸውም።
ግን ግን እኒህ ገጣሚያን ከበዓላት ሁሉ በተለየ ትንሳኤ እና ተዛማጅ ክንውኖቹ እንደምን የንሸጣቸው ምክንያት ሆነ?*
“እኔን እንድጽፍ ያደረገኝ ትልቁ ሃሳብ የጌታችን መከራው፣ የደረሰበት ስቃይ ነው” የሚለው ገጣሚ እና ደራሲ ኤፍሬም ስዩም ነው።
በትንሳኤ ሰሞን ተደጋግሞ የሚደመጠውን “የጅራፍ ንቅሳት” የተሰኘ ግጥሙን መነሻ ሲያብራራም፣ “በእርሱ ስቃይ እኛ ተፈውሰናል፤ ድነናል። ስለዚህ እኔ ልደሰት ነው የሚገባኝ፤ ይሄ ሁሉ መሰዋዕትነት ለእኔ ነው የተከፈለው። ያንዳንዱ ሰው ይሄን ደስታውን በተለያየ መንገድ በመዝሙር፤ በሥዕል ይገልጻል። እኔ ደግሞ የምገለጸው በመጻፍ ነው” ይላል።
ገጣሚ ደምሰው መርሻ በበኩሉ፣ እንዴት ትንሳኤ ለግጥም ሥራው መነሻ እንደሆነው ሲያስረዳ “ከሞት በኋላ የሚመጣን ሕይወት ማሰብ፤ ከሽንፈት በሁዋላ የሚመጣን ድል፤ ከውድቀት በኋላ መነሳትን የመሳሰሉ ብዙ ነገሮችን ያመለክታል። ይህ ክስተት የሰው ልጅ አዲስ የድኅነት መንገድ ያገኘበት እና ሞት የተሸነፈበት በመሆኑ ነው” በማለት ይናገራል።
በደምሰው የግጥም አልበም ውስጥ የተካተተው “የክርስቶስ ሐሙስ” ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በተጋራው የመጨረሻ እራት ላይ በአዕምሮው ይብሰለሰሉ የነበሩ ጉዳዮችን ያስቃኛል።
“ልቤን ፍርሃት ናጠው ሲመጣ ሰዓቱ፣
ሊፈጸም ነው መሰል የመጻፍ ትንቢቱ፣
ጭፍሮቼን አየሁኝ፣
የማውቃው መልካቸው ለአሁን የተረሳኝ፣
ማን ይሁን ባለንጀር፣ አሳልፎ ሰጪ ዛሬስ የሚስመኝ።” . . . እያለ ይወርዳል - የደምሰው ግጥም።
ደምሰው በዚህ ሥራው በቅዱሳን መጽሐፍት ላይ በተጠቀሰ ክንውን ላይ የራሱን የገጣሚነት ዐይነ-ህሊና (Imagination) ጨምሮ ነው የሚተርክልን።
ዐይነ-ህሊናን በመጠቀም ጉዳይ ደምሰው ብቸኛ አይደለም። ገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ ኪናዊ ለዛ ለማላበስ እንደተደረገ ጥረት ትቆጥረዋለች፤ በምትታወቅበት “የይሁዳ ሚስት” በተሰኘው ግጥም ውስጥም ተጠቅማዋለች።
“በእኔ ግጥም ውስጥ ያለው ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ አይደለም። የኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብዙ መጽሐፍት እና አንድምታዎች አሏት፤ የእኔ የግጥም ማጠንጠኛም እኒህን መጽሐፍት መሠረት ያደረጉ አስተምህሮዎች ናቸው” ትላለች።
ምልዕቲ በግጥሟ ዐይነ-ህሊናን እና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ለማስማማት ያለውን የቤት ሥራንም ታጋራለች፣ “እንደሚታወቀው የይሁዳ ሚስት የሚል የስቅለት ግጥም ነው እኔ ያለኝ። ስለይሁዳ ቀደም ብሎ የነበረውን እና በቤተክርስቲያን ዘንድ ሲነገር የነበረውን ታሪክ ነው መነሻ ያደረግኩት።
“ግጥሙን ከመጻፌ በፊት የአስራ ሁለቱን ሃዋሪያት የመጀመሪያ ሙያቸውን ለማወቅ ጥረት አድርጌያለሁ፣ እሱም ጊዜ ፈጅቶብኛል። በዚህ ሂደት ውስጥ የእኔ ባለታሪክ ይሁዳ የመጀመሪያ ሥራው ወታደርነት እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ። ግጥሙ የተጻፈው በይሁዳ ሚስት (እናት) ምናብ ውስጥ ራሴን በማስቀመጥ ነው፣ እሷን ሆኜ ነው የጻፍኩት” በማለት ታክላለች።ሰ
ዓለማዊ አረዳድን እና መንፈሳዊ ሀሳቦችን ማስማማት የገጣሚያኑ የእጅ አዙር ፈተና መሆኑ አይካድም። እንዲህ ባለው ወቅትስ ገጣሚያኑ ምን ያስቀድማሉ?
“አንድ ሃሳብ ወደ ጽሑፍ ሲቀየር በራሱ መንፈሳዊ ነው? ሚል ጥያቄ በግሌ አለኝ” የሚለው ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም “ስለክርስቶስ ስንናገር ስለ እናት ፍቅር ተናግረናል፤ ስለ ይሁዳ ክህደት ተናግረናል፤ ለሰው ልጆች ስላለው ጥልቅ ፍቅር ተናግረናል።
“ምናልባት መነሻ ሃሳባችን ሥጋ ለበስ ወይም ዓለማዊ ሊሆን ይችላል እንጂ በዚያ ውስጥ የምንናገራቸው ነገሮች ጥልቅ የሆነውን መነካት መግለጫ ነው” ይላል።
ገጣሚ ደምሰው መርሻ በበኩሉ የማስማማት ሂደቱ በግጥሙ ጥንስስ ወቅት መታሰብ ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ያምናል “ከባዱ ነገር መጀመሪያ ሃሳቡን የቱ ጋር እንደሚቀመጥ መወሰኑ ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሁሉን ነገር ግጥም ማድረግ አይቻልም።
“ነገር ግን አንድ ሃሳብ ወደ ግጥም ሲቀየር እዚህ ጋር መልዕክቱ ይሄ ነው፤ የተመሰለው በህይወት ነው፤ በድኅነት ነው ብሎ ማስቀመጥ ያሰፈልጋል። ስለዚህ ነገሮች ሁሉ የጋራ መግባቢያቸውን መፈለግ ነው ዋናው ነገር እንጂ፣ ከዚያ በኋላ ብዙ አይከብድም” በማለት ዕይታውን ያስቀምጣል።
ገጣሚያኑ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በዓል በሆነው የትንሳኤ በዓል ሰሞን ግጥሞቻቸው ተደጋግመው ይነሱ እንጂ፣ በሌሎች ዓለማዊ ግጥሞቻቸው ያፈሯቸው የሌላ ዕምነት ተከታዮችም አሏቸው።
መንፈሳዊ ትርክት ላይ መሰረት አድርገው የተፃፉ ሥራዎቻቸውን እኒህ ተከታዮቻቸው በምን አግባብ እንዲረዱላቸው ፈልገው ይሆን?
“ቅዱስ ቁርአንም ሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይሁን፣ አንዳንዴ ገጣሚው የተነሳበትን መንገድ በአግባቡ የሚገልጽ ከሆነ ከአድማጮች ጋር አይጠፋፋም። ብዙዎቹ ሃሳቦች ሃይማኖትን አይደለም የሚሰብኩት፤ የተለያዩ ሃሳቦችን እና ፍልስፍናዎችን እንጂ” ይላል ገጣሚ ደምሰው መርሻ።
ገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ በበኩሏ ከሃይማኖቱ ተከታዮች ውጭ ያሉ አድማጮች ሊገጥማቸው የሚችለውን ያለመረዳት ችግር ትቀበለዋለች።
“ለኦርቶዶክስ አማኞች የእኔ ሃሳብ አዲስ አይደለም፣ ለመቀበልም አይቸግራቸውም ብዬ አስባለሁ። የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ግን ግጥሙን እንደ ግጥም ለመረዳት እነዚህን መጽሐፍት ትንሽ ማገላበጥ ያስፈልግ ይሆናል። ሆኖም ግጥሙ በራሱም ታሪክን ስለሚናገር የሃይማኖት ተከታይ ባይሆንም ይዘቱን መረዳት የሚቻል ይመስለኛል።”
“ከጀርባህ ላይ ያለው የጅራፍ ንቅሳት፣
እኛን የመውደደህ የዘላለም ብስራት፣
የፋሪስ የሳዱቅ ያለማመን ደባ፣
የጲላጦስ ግርፊያ የሄሮድስ ካባ…”
እያለ እየሱስ ክርስቶስ በሰሞነ ህማማት ያየውን ፍዳና እንግልት በቃላቱ ስሎ፣ በድምጹ አጅቦ ለአድማጭ እንካችሁ ያለው ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ መልዕክቱ ሁሉም አይነት አድማጮች የሚረዱት መሆኑን፣ ሆኖም አድማጮች (ተከታዮች) ግጥሙን ለሚያመልክው ፈጣሪው እንዳቀረበው የግል መባ እንዲያዩለት እንደሚፈልግ ያስረዳል።
“ብዙ የክርስትና ዕምነት የማይከተሉ ጓደኞች አሉኝ። አብዛኞቹ የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው። ሃሳቤን በጣም የሚገርምና የሚያም ነው ይሉኛል። ይህን ህመም ለመረዳት ክርስቲያን መሆን አይጠበቅባቸውም። እኔ ሃሳቡን በተረዳሁበት መንገድ እነሱም ይረዱታል።
“እንደ አንድ የሥነ ጽሁፍ ሰው እኔ ለማምነው ክፍል ሃሳቤን መሰዋዕት አድርጌ አቀርባለሁ። ይህ ለፈጣሪዬ ቀረብ መሰዋዕት ነው። አብዛኛዎቹ የሃይማኖቱ ተከታይ ያልሆኑት ሰዎች ግን ‘ሃሳቡ በጣም ደስ ይላል!’ ይሉኛል። ማንም ላይ ሃሳቤን እየጫንኩኝ ሳይሆን የተሰማኝን እየገለጽኩኝ ነው” ሲል ይደመድማል - ኤፍሬም።
***
ማስታወሻ፡ ከገጣሚያኑ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ የተካሄደው እና ጽሁፉ የተዘጋጀው ከአራት ዓመት በፊት ነበር። የተወሰነ የአርትኦት ሥራ ተደርጎበት በድጋሚ የቀረበ ነው።