በርካቶች የገናን በዓል ለማክበር ቤተልሔም ደረሱ

በቤተልሄም የገናን በዓል ለማክበር የመጡ ዜጎች

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock

ታትሟል

ዛሬ ታህሳስ 16፣ 2015 ዓ.ም  የሚከበረውን የእየሱስ ክርስቶስ ልደትን በዓል ለማክበር በርካታ የዓለማችን ዜጎች ቤተልሔም ደረሱ።

ቤተልሔም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በዛሬው ዕለት የገናን በዓል ያከብሩባታል ተብሎም ይጠበቃል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ክርስቲያኖች ቅድስት ወደምትባለው ስፍራ የሚያደርጉት ጉዞም ተስተጓጉሎ ነበር።

የቤተልሔም ከተማም ምጣኔ ኃብትም ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ክፉኛ ተመትቶታል።

ለሁለት ዓመታት ያህል ክብረ በዓላት ቀጥ ብለውባቸው የነበሩ የቤተልሔም ጎዳናዎች በምዕመናን ተጨናንቀዋል።

 ነገር ግን ቁጥሩ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ከነበረው ከአውሮፓውያኑ 2019 ጋር ሊመጣጠን አልቻለም።

ከሌሎች አገራት ከመጡ ምዕመናን በተጨማሪ ፍልስጥኤማውያን ክርስቲያኖችም በ4ኛው ክፍለ ዘመን በተገነባችው ቤተ ክርስቲያን በሚደረገው የእኩለ ሌሊት ቅዳሴ ላይ ይገኛሉ።

በእስራኤል ወረራ ስር ባለችው ዌስት ባንክ ክብረ በዓሉ በብጥብጥና ግጭት በታጀበ መልኩ ነው እየተከበረ ያለው።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በሚጨወቱ የስካውት ባንዶች ታጅበው ከእየሩሳሌም ተነስተው ወደ መንገር አደባባይ ተምመዋል። የእየሱስ ክርስቶስ ትውልድ ስፍራ ናት ተብሎ በሚታመንበት ቦታም ላይ በተገነባችው ቤተክርስቲያን በሚደረገው የእኩለ ሌሊት ቅዳሴም ላይ ይገኛሉ።

ከገሊላ እና ከጋዛ ሰርጥ የመጡ ፍልስጥኤማውያን ክርስቲያኖችን ጨምሮ ከዓለም ዙሪያ የመጡ ምዕመናን አሉ።

ምንም እንኳን የምዕመናኑ ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2019 ከታየው አኃዝ ቢያንስም ጎዳናዎች በምዕመናን ተሞልተዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ሆቴሎችም ሞልተዋል።

ምንም እንኳን በአካባቢው በንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች ምጣኔ ኃብቱ እንደሚያገግም ብሩህ ተስፋን ቢሰንቁም በቅርቡ በእስራኤላውያንና ፍልስጥኤም ያለው ግጭት መባባስ እንዲሁም የመጪው የእስራኤል ቀኝ አክራሪ መንግሥት ፖሊሲ ስጋትን አጭሯል።

በእስራኤል ታሪክ አክራሪ ቀኝ ክንፍ ተብሎ የሚታመነው አዲሱ መንግሥት የቤንጃሚን ኔታንያሁ ወደ ታሪካዊ ስድስተኛ የስልጣን ዘመን መመለሳቸውንም ያመላከተ ነው።