ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ በገና በዓል መልዕክታቸው "ነጻነት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል" አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በገና በዓል መልዕክታቸው ህዝቡ የሩስያ ጥቃቶችን በመቋቋም ረገድ ጸንተው እንዲታገሉ አሳሰቡ።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት ዛሬ ታህሳስ 16፣ 2015 ዓ.ም በበርካታ አገራት የሚከበረው የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ነው።
በገና ዋዜማ፣ ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ንግግር “ነፃነት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ባርነት ደግሞ ከዚያም የበለጠ ዋጋ አለው” ብለዋል።
የሩስያ ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያንን ያለ ኤሌክትሪክ ሃይል፣ ማሞቂያ እና ውሃ እንዲቋረጥባቸው አድርጓል።
ቅዳሜ ዕለት በዩክሬን ደቡባዊ ኬርሶን ከተማ ሩስያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 10 ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
68 ሰዎች መቁሰላቸውን የክልሉ ባለስልጣናት ገልጸው የአካባቢው ነዋሪዎች በአስቸኳይ ደም እንዲለግሱ ጠይቀዋል።
ሩሲያን “አሸባሪ ሃገር” ሲሉ የገለጹት ዜለንስኪ የሩስያ ወታደሮችን “ለማስፈራራትና ለደስታ ሲሉ ገድለዋል” ሲል ከሰዋቸዋል።
በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ባሰፈሩት መግለጫ፣ “ዓለም ማየት አለበት። የምንዋጋው ከክፉ ሰይጣን ጋር መሆኑን መረዳት አለበት” ሲሉ በአስከሬኖች እና በተቃጠሉ መኪኖች የተሞሉ ጎዳናዎች ምስሎች አሳይተዋል።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 24 ወረራውን ከጀመረች በኋላ በሩሲያ የተያዘችው ብቸኛዋ የክልል ዋና ከተማ ኬርሰን ባለፈው ወር በዩክሬን ኃይሎች ነፃ ወጥታለች።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ በዲኒፕሮ ወንዝ ግራ ዳርቻ ላይ በተቀመጡ የሩሲያ ኃይሎች በተደጋጋሚ ዒላማ ተደርጋለች።
በጥቃቱ ሠላማዊ ሰዎችን ዒላማ አለማድረጓን ሞስኮ ደጋግማ ገልጻለች።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሩስያ ወታደሮች የዩክሬን ወሳኝ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እየመቱ መሆናቸውን በቅርቡ አምነዋል።
አብዛኞቹ ዩክሬናውያን የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በመሆናቸው የሃገሪቱ የልደት የበዓል ታህሳስ 29 ይከበራል።
ይሁን እንጂ በርካታ ምዕመናን በዓለማችን ካሉት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ጋር ቀኑን ታኅሣሥ 16 ቀን እያከበሩት ይገኛሉ።
ዜለንስኪ ቅዳሜ ዕለት ለህዝቡ ባደረጉት የቪዲዮ ንግግር “በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ጸንተናል። ጥቃቶችን፣ ዛቻዎችን፣ የኒውክሌር ጥቃቶችን፣ ሽብርንና የሚሳኤል ጥቃቶችን ተቋቁመናል። የምንዋጋውን ስለምናውቅ በዚህ ክረምትም ጸንተን እንቆያለን” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, UKRAINE'S PRESIDENTIAL OFFICE
"በዓላቶቻችንን እንደሁልጊዜውም እናከብራለን! ፈገግ ብለን ደስታችንን እንገልጻለን። ይህ እንደ ሁልጊዜው ይሆናል። ልዩነቱ አንድ ነው። ተአምር አንጠብቅም። ሁሉንም ነገር ራሳችንን እንፈጥራለን።”
በኪዬቭ የሚገኘው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሁጎ ባቼጋ እንደሚለው ለብዙ ዩክሬናውያን የገና በአል በጨለማ እና በብርድ ይከበራል።
11 ወር የሞላው ጦርነት ከጉዳቱ ይልቅ የበለጠ እንዲጠናከሩ እንዳደረጋቸው ዩክሬናውያን እንደሚገልጹ ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።
ቅዳሜ ዕለት ጦርነቱ ሲቀጥል በዩክሬን ምሥራቃዊ ዶንባስ ግዛት የሩስያ ወታደሮች ባክሙትን የተሰኘችውን ስትራቴጅያዊ ከተማ አጥቅተዋል።












