በትግራይ የነበረው የረሃብ አደጋ ስጋት መቀልበሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, WFP/ETHIOPIA
ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል አንዣቦ የነበረው የረሃብ አደጋ ስጋት መቀልበሱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ይህን ያለው በትግራይ ክልል ለሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ መቻሉን ተከትሎ ነው።
የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ የረሃብ አደጋ ስጋቱ ተቀልብሷል ማለታቸውን ትዊተር ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ተችተውታል።
በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው እና ለ20 ወራት የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት በተለይ በትግራይ ክልል ከፍተኛ የሚባል ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ ድርጅቶች በክልሉ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲሉ ተደጋጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲያወጡ መቆየታቸው ይታወሳል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃላፊ ኤድሪያን ቫንዳክናብ ዓርብ ሐምሌ 08/2014 ዓ.ም. ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ድርጅታቸው የሰብዓዊ እርዳታውን ማድረስ በመቻሉ፤ በትግራይ ክልል ተከስቶ “የረሃብ አደጋው ስጋት ተቀልብሷል” ብለዋል።
“ይህ ማለት ግን ሁኔታዎች በዚህ ሁኔታ ይቀጥላሉ ማለት አይደለም” ይላሉ ኤድሪያን ቫንዳክናብ። አሁን ያለልው ሁኔታ እንዲቀጥል ለሰብዓዊነት ሲባል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ እንዲደርስ ስላቻለን፤ ይህ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ለ2.1 ሚሊዮን ሰዎች ምግብ ለማድረስ ታቅዶ ለ1.1 ሚሊዮን ሰዎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ ማድረሱን ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የህወሓት ከፍተኛ አመራሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በትዊተር ገጻቸው እንደጻፉት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ በትግራይ ክልል የነበረው የረሃብ አደጋ ስጋት ተቀልብሷል መባሉን አልተቀበሉትም።
አቶ ጌታቸው ለዘጠን ወራት ወደ ክልሉ የሚገባው እርዳታ ተቋርጦ መቆየቱን ጠቅሰው፣ አቅርቦቱ መልሶ ከተጀመረ ስድስት ሳምንታት እንደሆነና፣ ያለውን እርዳታ ለተረጂዎች ለማድረስ የነዳጅ እጥረት በመኖሩ ችግሩ እንዳለ አመልክተዋል።
በዚህም ሳቢያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ለቢቢሲ የረሃብ አደጋው ተቀልብሷል ብለው መናጋራቸውን “ኃላፊነት የጎደለው” ብለውታል።
መጋቢት 2014 ዓ.ም. የፌደራሉ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ የሰብዓዊ እርዳታ በተሻለ መጠን ወደ ትግራይ ሲገባ መቆየቱ ተዘግቧል።
ኃላፊው ኤድሪያን ቫንዳክናብ ይህ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የእርሳቸው እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በሰመራ-መቀለ ኮሪዶር በኩል ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ከባድ መኪኖች ትግራይ መግባታቸውን ገልጸዋል።
“ጥሩ እና መጥፎ ዜናዎች አሉ። ጥሩ ነገሩ፤ ለሰብዓዊነት ሲባል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት እየተከበረ ነው” ያሉት ኃላፊው፤ ይህም የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች ምግብ እና መሠረታዊ ቁሶችን ማድረስ እንዳስቻለው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፀጥታ ሁኔታ፣ የተጨማሪ ፈንድ ጉዳይ እና የነዳጅ አቅርቦት ግን በእርዳታ አቅርቦት ሥራው ላይ አሳሳቢ ሆነው መቀጠላቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
ለ20 ወራት የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት በሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ላይ ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ኤድሪያን ቫንዳባክ ያስረዱ ሲሆን፤ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር አሁንም ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊ ኮሪደሮች መስፋፋት አለባቸው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ፤ ድርጅቱ መሠረታዊ የሚላቸውን አቅርቦቶችን ለማድረስ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።
“ተጨማሪ ፈንድ እንፈልጋለን። ገንዘብ እየጨረስን ነው። የአካባቢዎቹ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እንዲያነሰራራም መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ እንፈልጋለን” ብለዋል።
“ከ20 ወራት ጦርነት በኋላ ሰዎች ያሏቸውን ሌሎች አማራጮች አሟጠዋል ወይም ሊያሟጥጡ ከጫፍ ደርሰዋል። ተጨማሪ እርዳታ ማድረሻ ኮሪደሮች ካልተከፈቱ፣ ተጨማሪ ፈንድ ካልተገኘ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ካልተጀመሩ ለውጥ እያመጣን ልንቀጥል አንችልም።”
“ነገሮች እየተከፈቱ ነው። ግን በቂ አይደለም” ያሉት ኃላፊው፤ ከተኩስ አቁሙ ስምምነት ወዲህ በአንዳንድ ቦታዎች ከሚያጋጥሙ የደኅንነት ስጋቶች በቀር እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳናደርስ ክልከላ አልተጣለብንም ብለዋል።
አብዛኛውን የትግራይ አካባቢዎች ተቆጣጥሮ የነበረው የፌደራል መንግሥቱ እና አጋሮቹ ጦር፤ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ክልሉን ለቆ ከወጣ በኋላ እንደ ቴሌኮም፣ የአሌክትሪክ ኃይል እና የባንክ አገልግሎቶች ተቋርጠው ይገኛሉ።
የነዳጅ እጥረት
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃላፊ ኤድሪያን ቫንዳክናብ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ ላይ የነዳጅ እጥረት ሌላው ፈታኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በመላው አገሪቱ የነዳጅ እጥረት እንደሚከሰት አስታውሰው፤ በትግራይም የነዳጅ እጥረት መኖሩ የሰብዓዊ እርዳታ ማከፋፈል ሥራው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።
“በአገሪቱ ያለው የነዳጅ አቅርቦት እየተሻሻለ ነው” ያሉት አድሪያን ቫንዳክናብ፤ በትግራይ በየወሩ የሚያስፈልገውን 2 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እንዴት ወደ ክልሉ ማድረስ ይቻላል የሚለውን ከባለሥልጣናት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከትግራይ በተጨማሪ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ለሚገኙ በርካታ ሰዎች መሠረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ ቆሶችን አድርሻለሁ ብሏል።
ጦርነቱ ያስከተለው ጉዳት
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች የተዛመተው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራን አስከትሏል።
የተባበሩት መንግሥታት በሦስቱ ክልሎች የሚገኙ ከ9 ሚሊዮን የማያንሱ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል ነበር።
ይህ የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም አስከትሏል።
የጎረቤት አገር ኤርትራ፣ የክልል ልዩ ኃይሎች ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው የትግራይ ኃይሎችን ሲወጉ ቆይተዋል።
በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች በሲቪል ሰዎች ግድያ፣ ማሰቃየት እና ማሰር፤ ጾታን መሠረት ባደረጉ ከፍተኛ የሰብዓዊ የጥሰቶች ተጠያቂ መሆናቸውን የመብት ተሟጋቾች ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ አመልክተዋል።
ጦርነቱ ተባብሶ ወደ አጎራባች ክልሎች ከተዛመተ በኋላ የእርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ መግባቱ ተቋርጦ በነበረበት ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል።
ከ20 ወራት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የሰላም ድርድር ሊያካሂዱ እንደሆነ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች መውጣት ጀምረዋል።
የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደራደሩ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመሩ 7 አባላት ያሉት ኮሚቴ ይፋ አድርጓል።












