ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእሲያዊቷ አገር በእባብ የሚነደፉ ሰዎች መጨመሩን ተከትሎ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ታዘዙ
በእሲያዊቷ አገር ባንግላዴሽ በእባብ የሚነደፉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ተከትሎ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተላለፈ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዳይ በሆኑ የእባብ ዝርያዎች የሚነደፉ ሰዎች ቁጥር መጨመር በመላው ባንግላዴሽ ዜጎችን ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ከትቷል።
ባለፉት ሳምንታት በእባብ የሚነደፉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ በባንግላዴሽ ዋነኛ የማሕበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል።
የአገሪቱ መንግሥት በመላው አገሪቱ ያሉ ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች በእባብ ለተነደፉ ሰዎች የሚሰጡ መድሃኒቶችን አሟልተው እንዲይዙ መመሪያ ሰጥቷል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ላለ ሴን በእባብ የተነደፈን ሰው በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመወሰድ ነዋሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በገጠራማ ባንግላዴሽ የሚገኙ ሆስፒታሎች ራሰል ቫይፐር ተብሎ በሚጠራ የእባብ ዝርያ ተነድፈው ለሕክምና የሚመጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ሪፖርት አድርገዋል።
ይህ በደቡብ እሲያ አገራት የሚገኘው የእባብ ዝርያ ገዳይ ነው።
ይህ እባብ ብዙ ጊዜ አይጦችን የሚመገብ ሲሆን በተለይ ደግሞ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ወደ ሰዎች መኖሪያ መንደሮች ውስጥ ይገባል።
እአአ 2023 ላይ በባንግላዴሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእባብ ተነድፈዋል። ከእነዚህ መካከል 7ሺህ የሚሆኑ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ራስልስ ቫይፐር በተባለው የእባብ ዝርያ የሚነደፉ ሰዎች በፍጥነት የሕክምና እርዳታ የሚያገኙ ከሆኑ በሕይወት የመትረፍ ዕድል አላቸው።
ይህ የእባብ ዝርያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከባንግላዴሽ ለመጥፋት የተቃረበ የእባብ ዝርያ ነው ተብሎ ታውጆ የነበረ ቢሆንም እንደገና በመመለስ ከፍተኛ የጤና ስጋት ሆኗል።
ተመራማሪዎች ይህ በደረቅ እና ሞቃታማ አካባቢዎች ብቻ ይኖር የነበረው የእባብ ዝርያ አሁን ላይ በተለያዩ የአየር ጸባይ ሁኔታ ውስጥ መኖርን በመላመድ በ25 የባንግላዴሽ ግዛቶች መስፋፋቱን ይገልጻሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት በእባብ መነደፍ ችላ ከተባሉ የጤና ጠንቆች መካከል አንዱ መሆኑን በመግለጽ ለእባብ ንድፊያ ትኩረት መስጠቱን ይገልጻል።