ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለመላክ ማመንታቷን ከአሜሪካ ሾልኮ የወጣ መረጃ አሳየ
ከአሜሪካው ፔንታጎን ሾልከው የወጡ ሰነዶች በደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መላክን በተመለከተ ስለነበረው ውይይት ይፋ አደረገ።
ቢቢሲ የተመለከተው ሚስጥራዊ ሰነድ አሜሪካ ለአስርት ዓመታት አጋር ወይም ወዳጅ የምትላትን ደቡብ ኮሪያን ስትሰልል እንደነበረም ፍንጭ የሰጠ ነው።
ስለ ዩክሬኑ ጦርነት፣ የአሜሪካ አጋሮች እንዲሁም ቻይናንም በተመለከተ ሰነዱ መረጃዎችን አካቷል።
ሾልኮ የወጣው ይህ መረጃ ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ እና ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያበላሽ የሚችል አቅም እንዳለውም ተጠቅሷል።
ደቡብ ኮሪያ የወጣውን መረጃ እየመረመርኩ ነው ብትልም በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤቷ ውስጥ የሚደረጉ ግላዊ ንግግሮችን ለመጥለፍ እንደማይቻል አስታውቃለች። ሆኖም የተባለው ውይይት ከምድር በታች ባለው ጽህፈት ቤቱ ውስጥ የተካሄደ ሊሆን አይችልምም ብላለች።
ዋሽንግተን ይህንን መረጃ ያሾለከውን አካል ለማጣራት እየጣረ መሆኑን አስታውቆ ፔንታጎን በበኩሉ መረጃው ለሃገር ደኅንነት ከፍተኛ አደጋን ጋርጧል ብሏል።
ቢቢሲ የተመለከተው ይህ ሰነድ ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ማመንታት ውስጥ መግባቷን የሚያሳይ ነው።
አሜሪካ ዩክሬንን ለማስታጠቅ ደቡብ ኮሪያን ስትገፋ የቆየች ሲሆን ነገር ግን በጦርነት ላይ ላሉ አገራት የጦር መሳሪያ አቅርቦት የማያሰጠውን ፖሊሲዋን በመጥቀስም ስትቃወም ቆይታለች።
ባለፈው ዓመት ደቡብ ኮሪያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተሟጠጠውን የጦር መሳሪያ ክምቷን ለመሙላት የከባድ መሳሪያ መተኮሻዎችን ለአሜሪካ ለመሸጥ ተስማምታ ነበር።
ሆኖም እነዚህን መተኮሻዎች አሜሪካ ለዩክሬን እንዳትሰጥና ለራሷም እንድትይዘው ደቡብ ኮሪያ የስምምነቱ አካል እንዲሆን አጽንኦት ሰጥታለች። ሾልኮ የወጣው ሰነድ እንደሚያሳየው የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ስምምነቱ እንዳሳሰበው እና አሜሪካ እነዚህን የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን አሳልፋ ልትሸጥ እንደምትችልም መጠርጠሩን ያሳያል።
ሰነዱ በሁለቱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ከፍተኛ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪዎች መካከል ለአንድ ወር ያህል የተደረገውን ሚስጥራዊ ውይይት በዝርዝር ያካተተ ነው።