በሲዳማ ክልል "መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ጥረት" በማድረግ የተጠረጠሩት ባለሥልጣን ያለመከሰስ መብታቸው ተነሳ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሲዳማ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ በክልሉ መንግሥት ላይ "በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ጥረት በማድረግ" እንዲሁም "በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ግዥ እና ዝውውር" ተባባሪነት ተጠርጥረው ያለመከሰስ መብታቸው ተነሳ።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑትን የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ያነሳው ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ ነው።

በአስቸኳይ ጉባኤው በክልሉ ካሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ አለማየሁ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የውሳኔ ሀሳብ እንደቀረበ የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የውሳኔ ሀሳቡ የቀረበባቸው አቶ አለማየሁ ከሲዳማ ክልል ምስረታ አንስቶ በክልሉ ከፍተኛ ኃላፊነት እርከን ላይ የቆዩ ናቸው።

የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት በክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቶ ማሩ፤ ባለሥልጣኑ የተጠረጠሩት በኃላፊነት ላይ እያሉ ፈጽመዋቸዋል ከተባሉ የወንጀል ድርጊቶች ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል።

አቶ አለማየሁ ከተጠረጠሩባቸው የወንጀል ድርጊቶች መካከል "የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲመሩ በነበሩበት ጊዜ ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ግለሰቦችን በግፍ አስሮ ማሰቃየት" የሚለው ይገኝበታል።

የታሰሩ ግለሰቦችን "ለማስለቀቅ ከፍተኛ እጅ መንሻ መቀበልም" ባለሥልጣኑ የተጠረጠሩበት ሌላኛው ድርጊት ነው።

የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው፤ "ሕገ ወጥ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ፈቃድ መስጠት" እንዲሁም "ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ግዥና ዝውውር እንዲካሄድ መፍቀድ" የሚሉ ውንጀላዎችን ቀርበውባቸዋል።

"የግሉን ጥቅምን መሰረት" በማድረግ በክልሉ ውስጥ "ሕገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ ማድረግ" የሚለውም በፍትህ ቢሮ የቀረበ ሌላኛው ጥርጣሬ ነው።

አቶ አለማየሁ በክልሉ መንግሥት ላይ "መፈንቅለ መንግሥት" ለማድረግ "በመጣር" እንደተጠረጠሩ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮው አስታውቋል።

የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው፤ "በተደጋጋሚ በክልሉ መንግሥት ላይ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ጥረት" ሲያደርጉ እንደነበር የፍትህ ቢሮ ኃላፊው አቶ ማቶ ገልጸዋል።

"በተለያዩ ሕገ ወጥ መንገዶች ለራሱ ጥቅም በርካታ ገንዘብ መሰብሰብ" የሚለውም አቶ አለማየሁ ከተጠረጠሩባቸው "ዋነኛ ነጥቦች" መካከል እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።

የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ "ከመቅረቡ በፊት" የወንጀል ድርጊቶቹን በተመለከተ "ከተለያዩ አካላት መረጃዎች" እንደተሰበሰቡ እና "ተገቢው የማጣራት ስራ" እንደተከናወነ መገለጹን የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በመረጃው አስፍሯል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት በቀረበለት የአቶ አለማየሁን ያለመከሰስ መብት የማንሳት ውሳኔ ሀሳብ ላይ "በስፋት እንደተወያየ" እና በዚህም "የግለሰቡን በርካታ የወንጀል ድርጊቶችን" እንደተነሱም ተጠቅሷል።

ከዚህ ውይይት በኋላም ምክር ቤቱ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ "በሙሉ ድምጽ" እንደወሰነ ተገልጿል።

ሲዳማ ክልል በከፍተኛ ባስልጣንን ከኃላፊነት አንስቶ በወንጀል ድርጊቶች ተጠያቂ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ጸጋዬ ቱኬ ሐምሌ 2015 ዓ.ም. ከኃላፊነት ከተነሱ በኋላ በቁጥጥር ስር ውለው ተከስሰዋል።

በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉት አቶ ጸጋዬ፤ የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የወሰነባቸው ባለፈው መጋቢት ነበር።