ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት ጎሎች ባስቆጠረበት ጨዋታ ክብረ ወሰን ሰበረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በወንዶች እግር ኳስ ለብሔራዊ ቡድን በርካታ ጊዜ የተሰለፈ ተጫዋቾች በመሆን የዓለምን ክብረ ወሰን ባለቤት ሆነ።
ሮናልዶ ሁለት ጎሎች ባስቆጠረበት ጨዋታ ፖርቹጋል ሊችትንስታይንን 4 ለምንም ረትታለች።
ሮናልዶ ለብሔራዊ ቡድኑ ብዙ ጊዜ በመሰለፍ ካዝመዘገበው ክብረ ወሰን ባለፈ 120 ጎሎችን ለአገሩ ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋች ነው።
የ38 ዓመቱ ሮናልዶ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገሩ የተሰለፈው በፈረንጆቹ 2003 ሲሆን፣ ባለፈው ኳታር ላይ በአምስት ዓለም ዋንጫዎች የተጫወተ ብቸኛው እግር ኳሰኛ ሆኗል።
ሮናልዶ ሐሙስ ምሽት በነበረው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በፍፁም ቅጣት ምት እና ከ16 ከ50 ውጭ ባገኛት ቅጣት ምት አስቆጥሯል።
በሳዑዲ አረቢያ ሊግ ለአል ናስር የሚጫወተው ሮናልዶ፣ በመጀመሪያው አጋማሽ ጎል ለማስቆጠር ሲታገል ታይቷል።
ፖርቹጋል በጃዎ ካንሴሎ ጎል አንድ ለባዶ እየመራች ከሜዳ ብትወጣም በሁለተኛው አጋማሽ በሮናልዶ ሁለት ጎሎች እና በበርናንዶ ሲልቫ ጎል ግጥሚያዎን 4 ለምንም ፈፅማለች።
ሮናልዶ በኳታር የዓለም ዋንጫ 196 ጊዜ በመሰለፈር ከኩዌቱ አጥቂ ባድር አል-ሙታዋ ጋር ክብረ ወሰን ቢጋራም፣ ፖርቹጋል ከውድድሩ ስትሰናበት ለብሔራዊ ቡድን ድጋሚ መሰለፉ አጠራጣሪ ሆኖ ነበር።
አምስት ጊዜ የዓለም ምርጡ ተብሎ ባሎን ዶር የተሸለመው ሮናልዶ በኳታር ከመጀመሪያ 11 አሰላለፍ ውጭ ተደርጎ ነበር።
ነገር ግን አዲሱ የፖርቹጋል አሠልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ፤ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል እና የመጀመሪያው ተሰላፊ እንዲሆን አድርገዋል።
ሮናልዶ ታሪክ መሥራት ቀጥሏል
ሮናልዶ አዲስ የፃፈው ታሪክ ዓለማችንን ካየቻቸው ታላቅ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆኑን የበለጠ የሚያጠናክር።
ፖርቹጋላዊው አጥቂ አምስት ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ፤ አራት ጊዜ የዓለም ክለቦች ዋንጫ፤ አንድ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ ጨምሮ በስፔን፣ በጣሊያን እና በእንግሊዝ የተለያዩ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።
ለስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ የተጫወተው ሮናልዶ ሁለት ጊዜ የፊፋ ምርጡ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።
ባለፈው ኅዳር ሮናልዶ 800 ጎሎችን ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኖ ተመዝግቧል።
የሮናልዶ ክብረ ወሰኖች፡
- የቻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ
- በርካታ ጊዜ በቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች የተሰለፈ
- በርካታ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች ያነሳ
- በሦስት የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜዎች ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋች
- በርካታ ጊዜ በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ የተሰለፈ
- በአውሮፓ ዋንጫ በርካታ ጎሎችን ያሰቆጠረ
- ለብሔራዊ ቡድን በርካታ ጎሎች ያስቆጠረ
- በወንዶች እግር ኳስ ለብሔራዊ ቡድን 10 ሃት-ሪክ የሠራ የመጀመሪያው ተጫዋች












