“የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ለሙስሊሞች የተመቸ ሊግ ነው” የኤቨርተኑ ዱኩሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው ቅዱሱ የረመዳን ፆም ሐሙስ ይጀምራል።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እና በተቀሩት ሦስቱ የእንግሊዝ እግር ኳስ ውድድሮች ውስጥ በሚሳተፉ ክለቦች እና አካዳሚዎቻቸው ውስጥ በአጠቃላይ 253 ሙስሊም ተጫዋቾች አሉ።
ኑጁም ስፖርትስ የተሰኘው የመረጃ ቋት እንደሚለው ይህ ከጠቅላላው ተጨዋቾች ሲሰላ 5 በመቶ ነው።
የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ እግር ኳስ ተጫዋቾች የሥልጠና እና ጨዋታ ሰዓታቸውን አጨናንቀው ይህን ወር በፆም እና ፀሎት ያሳልፋሉ።
“ረመዳንን ሁሌም እወደዋለሁ” ሲል የኤቨርተኑ አማካይ አብዱላዬ ዱኩሬ ለቢቢሲ ይናገራል።
“አንዳንድ ጊዜ በፀደይ ወቅት ይሆን እና ውድድር ከመጀመሩ በፊት ስለምንፆም ትንሽ ይከብዳል። ነገር ግን እኔ አንድም ጊዜ ችግር ስላላጋጠመኝ፤ ዕድለኛ ነኝ።”
ዱኩሬ፤ “እምነቴ በሕይወቴ በጣም አስፈላጊው ነገር ነው” ይላል።
“ቅድሚያ የምሰጠው ለእምነት ነው፤ ከዚያ ሥራ ይመጣል። ሁለቱን አንድ ላይ ማስኬድ ይቻላል። እኔ እሱን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ።”
ዱኩሬ በትርፍ ጊዜው ወደ መስጂድ በመሄድ ፀሎቱን ያደርሳል፤ ቤቱም ቢሆን እምነቱን እንደማይረሳ ይናገራል።
“እምነት ባይኖረኝ እዚህ አልገኝም ነበር”
ዱኩሬ፤ ከማሊያውያን ቤተሰቦቹ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ነው የተወለደው።
በፈረንጆቹ 2016 ከፈረንሳዩ ክለብ ሬን ተሰናብቶ ለዋትፈርድ በመፈረም ሕይወትን በእንግሊዝ አንድ ብሎ ጀመረ።
በ2019 ቡድኑ ዋትፈርድ በኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ገጥሞ ተሸነፈ። በተመሳሳይ ዓመት ዋትፈርድ ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ወርዶ ወደ ታችኛው ሊግ ሲያቀና ኤቨርተን ዱኩሬን በ20 ሚሊዮን ፓውንድ የራሱ አደረገው።
በአሠልጣኝ ሾን ዳይሽ አመራር ከባድ ሥልጠና በኋላ ለቢቢሲ ቃለ-መጠይቅ የሰጠው የ30 ዓመቱ ዱኩሬ እምነቱ ምን ያህል ጥንካሬ እንደሚሰጠው ይናገራል።
“ቤተሰቦቼ በጣም ኃይማኖተኛ ናቸው። ከእነሱ ነው መልካም ሙስሊም መሆንን የተማርኩት። ይህ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። እምነቴ ብዙ ፈተናዎችን እንድሻገር አስችሎኛል” ይላል ዱኩሬ።
“በእግር ኳስም ይሁን በሌላው ሕይወት ብዙ ፈተናዎች ይገጥማሉ። እግር ኳስ የመውጣት እና የመውረድ ወድድር ነው። አንዳንድ ጊዜ ሳትጫወት ትቀራለህ፤ በሌላው ጊዜ ጉዳት ይገጥምሃል።
“እምነቴ እነዚህን ጊዜያት በጥንካሬ እንድሻገር አስችሎኛል። አምላክ ጥንካሬውን ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ።”

“ፕሪሚዬር ሊጉ ለሙስሊሞች የተመቸ ነው”
ዱኩሬ እና ቤተሰቡ በታላቁ ማንቸስተር ነው የሚኖረው። በአካባቢው ወደ ሚገኘው መስጂድ ዘወትር ያቀናል። ወደዚህ መስጂድ የሚያቀኑ የእስልምና እምነት ተከታዮም በደስታ እንደሚቀበሉት ይናገራል።
ይህ ስሜት ከመስጂድ አልፎ በፕሪሚዬር ሊጉ እና በአገረ እንግሊዝ በጠቅላላው እንደሚንፀባረቅ የሚናገረው ዱኩሬ እንግሊዝን “በአውሮፓ ካሉ ምርጥ አገራት አንዷ ናት” ሲል ይገልፃታል።
“እዚህ የተሻለ ነፃነት አለን። ተቀባይነት አለን። በፕሪሚዬር ሊጉ ሕይወትህን እንደፈቀድክ መኖር ትችላለህ። ማንም በእምነትህ የሚመጣ የለም። ይህ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው።”
“እኔ ፈረንሳይ ነው ተውልጄ ያደግኩት። ነገር ግን በፈረንሳይ እና በእንግሊዝ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። እንግሊዝ ትልቅ ምሳሌ መሆን የምትችል አገር ናት” ይላል ዱኩሬ።
“አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ማዳመጥ አለብን። እምነታቸው ለእነሱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። ይህ ምርጫ አይደለም። እምነታችን መቶ በመቶ ሊጠበቅ ይገባል።”
ዱኩሬ እንደሚለው ሁሌም ምኞቱ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ መጥቶ መጫወት ነበር። አሁን ደግሞ እስከሚቻለው ድረስ ቢቆይ ደስ ይለዋል።
“ፕሪሚዬር ሊጉ ለሙስሊም ተጫዋቾች የተመቸ ነው” ይላል።
“ፍፁሙ ሳላህ”
ዱኩሬም ሆነ የቡድን አጋሮቹ ሴኔጋላዊው ኢድሪሳ ጌዬ እና ቤልጂየማዊው አማዱ ኦናና የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው።
ሦስቱ አማካዮች በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጭ ጥምረታቸው ጠንከር ያለ ነው። በመልበሻ ክፍል ኢድሪሳ ኢማም በመሆን ፀሎት ይመራል። ዘወትር አርብ ደግሞ ጁምአን አብረው ያሳልፋሉ።
“ተመሳሳይ ቋንቋ እንናገራለን። አብረን በተመሳሳይ ሥፍራ ነው የምንጫወተው። ይህ ደግሞ የበለጠ እንድንቀራረብ አድርጎናል” ይላል ዱኩሬ።
“ሁሌም አብረን ነው ፀሎት የምናደርሰው። ኢድሪሳ በዕድሜም ስለሚበልጠን እና የተሻለ ምክር ስለሚሰጠን እሱ ነው የሚመራው።”
ዱኩሬ በእግር ኳስ የእሱ አርአያ ማን እንደሆነ ሲጠየቅ፣ የተቀናቃኙ ክለብ አጥቂ የሆኑትን እግር ኳስ ተጫዋቾችን መርጧል።
“ሳዲዮ ማኔ እና ሞሐመድ ሳላህን እወዳቸዋለሁ” ይላል ስለሁለቱ ሙስሊም አጥቂዎች እያወራ። ማኔ ወደ ባየርን ሙኒክ ከማቅናቱ በፊቱ ሁለቱ ተጫዋቾች የሊቨርፑል አጥቂ መስመር መሪዎች ነበሩ።
“በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለውን ልዩነት አውቃለሁ። ነገር ግን እሱን [ሞሐመድ ሳላህን] እንደሰው ልጅ እወደዋለሁ።”
እግር ኳሰኞች አርአያ መሆን እንዳለባቸው የሚናገረው ዱኩሬ፤ ሞሐመድ ሳላህ እዚህ ደረጃ እንደደረሰ ይናገራል።
“ለክለቡ ጥሩ እየሠራ ስለሆነ ሰዎች ይወዱታል። አልፎም ሰዎች ስለእስልምና ማወቅ ይፈልጋሉ። እሱ ለሁላችንም መልካም ምሳሌ የሆነ ፍፁም ሰው ነው።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“በረመዳን ሁሉንም ቀን ነው የምፆመው”
የኤቨርተን ሙስሊም ተጫዋቾች ዱኩሬ፣ ኦናና፥ ኢድሪሳ እና ቦስኒያዊው ግብ ጠባቂ አስሚር ቤጎቪች በረመዳን ወር ይፆማሉ።
የኤቨርተን ሥነ-ምግብ ክፍል ኃላፊ ሎይድ ፓርከር ተጫቸዋቾቹ እምንት እና ባሕላቸውን በማይነካ መንገድ ካርቦሃይድሬት አብዝተው እንዲመገቡ ይመክራል።
ንጋት አካባቢ ፆም ከመጀመሩ በፊት ገንፎ፣ እንቁላል አሊያም ዳቦ በማርማላትና ጭማቂ ይመገባሉ።
ከፆም በኋላ ደግሞ በሚንስትሮን ሾርባ ይጀምሩና ፓስታ አሊያም ሩዝ ይከተላል። ከዚያም ፍራፍሬ ይታከልበታል።
“በረመዳን ወቅት አንድም ቀን ሳልዘል ነው የምፆመው” ይላል ዱኩሬ። “ስለተላመድኩት እየቀለለኝ መጥቷል። ከ12 ወይም ከ13 ዓመቴ ጀምሮ ስፆም ነው የኖርኩት። ሰውነቴን በደንብ ነው የማውቀው። ጥሩ ቁርስ ከተመገብኩ ቀኑን ያውለኛል።”
በረመዳን ወቅት ሥልጠና አይጓደልም የሚለው ዱኩሬ፣ የክለቡ ሼፍ ሁሉንም አዘጋጅቶ እንደሚጠብቃቸው ይናገራል።
“በረመዳን ወቅት ቤተሰብ ተሰባስቦ ፆም ይፈታል። ይህን ወቅት እወደዋለሁ። አዳዲስ ሰዎች እንተዋወቃለን። ረመዳን ሙስሊሞች ከእምነታቸው ጋር እንዲቀራረቡ በጣም አስፈላጊ ወቅት ነው።”












