ትውልደ ሶማሊያዊቷ ኢልሃን ኦማር በድጋሚ አሸነፉ

ኤልሃን ኦማር ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው ምክር ቤት በድጋሚ ገብተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤልሃን ኦማር በሜንያፖሊስ ፊቭዝ ዲስትሪክት አሸንፈዋል
ታትሟል

በሜኔሶታ፣ ሜኒያፖሊስ፣ ፊቭዝ ዲስትሪክት ለሦስተኛ ጊዜ እጩ ሆነው የቀረቡት ትውልደ ሶማሊያዊቷ ኤልሃን ኦማር የሪፐብሊካን ተፎካካሪያቸውን ሲሲ ዴቪስን በመርታት በድጋሚ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት መግባታቸውን አረጋግጠዋል።

ኤልሃን ኦማር የሪፐብሊካኗን ተፎካካሪ ሲሲ ዴቪስን ያሸነፉት በከፍተኛ ድምጽ ልዩነት ነው።

ኢልሃን በአሜሪካ ታሪክ የመጀመርያዋ ትውልደ ሶማሊያዊት የምክር ቤት አባል ናቸው።

ኢልሃን የመጀመርያዋ ሒጃብ ለብሰው የምክር ቤት አባል የሆኑ እንዲሁም አፍሪካ ተወልደው የአሜሪካ ኮንግረስ በመሆን የመጀመርያ ሴት ናቸው።

ኢልሃን ለመጀመርያ ጊዜ በ2018 የምክር ቤት አባል ሲሆኑ ከሁለት ሙስሊም እንደራሴዎች አንዷ ለመሆን ችለው ነበር።

የኢልሃን ኦማር ቤተሰቦች ከሶማሊያ በስደተኝነት አሜሪካ የገቡ ናቸው።

ዛሬ በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዲሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች ተናንቀዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን የሕግ መምሪያ እና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች ተወካዮችን እንዲሁም አገረ ገዢዎችን ሲመርጡ ውለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከፍተኛ ፉክክር እየታየበት ባለበት በዚህ የ‘ሚድ-ተርም’ [አጋማሽ የሥልጣን ዘምን] ምርጫ ውጤቶች መገለጽ ጀምረዋል።

የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱን ለመቆጣጠር ሪፐብሊካኖች ከፍተኛ ተስፋን ሰንቀዋል። እየተሳካላቸውም ይመስላል።

የሕግ መወሰኛውን ምክር ቤትም ቢሆን በሪፐብሊካኖች የበላይነት ለመያዝ የአንድ እንደራሴ ብልጫ ብቻ በቂ ይሆናል።

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴዎች የሥራ ዘመን ስድስት ዓመት ቢሆንም ከጠቅላላው 100 መቀመጫዎች አንድ እጁ ለምርጫ ቀርቧል። ይህም በድምሩ 35 ወንበሮችን ይይዛል።

የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የእንደራሴዎች የሥራ ዘመን ደግሞ ሁለት ዓመት ብቻ ነው።

የዚህ ታችኛው ምክር ቤት 435 መቀመጫዎች ሲኖሩት ሁሉም ለውድድር ቀርበዋል።

ሪፐብሊካኖች የታችኛውን ምክር ቤት ለመቆጣጠር ከ435 ወንበሮች፣ 218 ወንበሮችን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ዜና እስኪጠናቀር ድረስ 198 መቀመጫዎች ከወዲሁ በሪፐብሊካኖች የተያዙ ሲሆን፣ ዲሞክራቶች 173 ላይ ናቸው።

ለጊዜው ሪፐብሊካኖች የታችኛውን ምክር ቤት ለመቆጣጠር የሚቀራቸው መቀመጫ 22 ብቻ ነው።

በሴኔት ደግሞ ዲሞክራቶች 48 መቀመጫ ሪፐብሊካኖች ደግሞ 47 መቀመጫዎችን ይዘው ተፋጠዋል።

ሴኔትን በበላይነት ለመቆጣጠር ከ50 መቀመጫዎች አንድ ተጨማሪ ወንበር ማግኘት በቂ ነው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ሁለቱ ፓርቲዎች እኩል 50-50 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ወንበርን ይዘው የነበረ ሲሆን የዚህ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሜላ ሐሪስ በመሆናቸው ዲሞክራቶች የአንድ ድምጽ ብልጫ ነበራቸው።

ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውድድር ከፍተኛ ትንቅንቅ እየታየ ያለው በኔቫዳ፣ ፔንሲልቬኒያ እና ጆርጂያ ግዛቶች ውስጥ ነው።

በጆርጂያ የዲሞክራቱ ራፋኤል ዋርኖክና የሪፐብሊካኑ ሚስተር ዎከር ከፍተኛ ፉክክር እያደረጉ ነው።

ይህ የጆርጂያ ምርጫ ውጤት እስኪለይለት ቀናት ሊወስድ ይችላል።

ይሁንና በፔንሲልቬኒያ የአገረ ገዢነቱን ቦታ የዲሞክራቱ ጆሽ ሻፒሮ አሸንፈዋል።

 ዶናልድ ትራምፕ እና ሮን ዴ ሳንቲስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቀጣይ ሪፐብሊካንን ወክለው ለፕሬዝዳንትንት ለመቅረብ ይፎካከራሉ የተባሉት ዶናልድ ትራምፕ እና ሮን ዴ ሳንቲስ

በ2024 የትራምፕ ከፍተኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት የፍሎሪዳው አገረ ገዢ ሮን ዴሳንቲስ ለአዲስ የሥራ ዘመን ድጋሚ አሸናፊነታቸውን አውጀዋል።

እኚህ ሰው የሪፐብሊካን አባል ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ግንኙነታቸው እየሻከረ መጥቷል።

ዴሳንቲስ ማሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪያቸውን ያሸነፉበት ሰፊ ልዩነት አነጋጋሪ ሆኗል።

በፔንሲልቬኒያ ግዛት ለሴኔት ከፍተኛ ፉክክር እያሳዩ ያሉት የዲሞክራቱ ፌተርማንና የሪፐብሊካኑ ዶ/ር ሜህሜት ኦዚ ናቸው።

ዶ/ር ኦዚ በርካቶች በቴሌቪዥን የጤና ትዕይንት አቅራቢነት ያውቋቸዋል።

አገረ ገዢው ፌተርማን በስትሮክ ህመም ከተጎዱ ወዲህ ተመልሰው በምርጫው ከፍተኛ ተፎካካሪ ሆነው ቆይተዋል።

የዚህ ግዛት ምርጫ ውጤቱ በሰዓታት ውስጥ ይፋ ይደረጋል።

የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ግን ከወዲሁ የማሸነፉን ተስፋ ለዲሞክራቱ ፌተርማን ሰጥቷል።

በሊዊዚያና ግዛት የሪፐብሊካኑ ሴናተር ጆን ኬኔዲ ዲሞክራቱን ተፎካካሪያቸውን በከፍተኛ ብልጫ አሸንፈዋል።

በኒው ሐምፕሻየር የዲሞክራቱ ሴናተር ማጊ ሐሰን የሴኔት መቀመጫን አሸንፈዋል።

በዋሺንግተን ግዛትም ዲሞክራቶች ተመሳሳይ ድል አግኝተዋል።

በኦሃዮ የሪፐብሊካኑ ጄዴ ቫንሽ ለሴኔት አሸናፊ ሆነዋል።

በቴክሳስ እና ፍሎሪዳ የአገረ ገዢነቱን ቦታ ሪፐብሊካኖች ቀንቷቸዋል።

እስከአሁን ባለው ለሕግ መምሪያ ምክር ቤት ዲሞክራቶች 142 ወንበሮችን አሸንፈዋል።

ሪፐብሊካኖች በአንጻሩ በከፍተኛ ብልጫ 179 መቀመጫዎችን ይዘዋል። ይህም ከ435 መቀመጫዎች መካከል መሆኑ ነው።

ሪፐብሊካኖች ከዚህ ጠቅላላ 435 መቀመጫዎች ውስጥ 218 መቀመጫን ካሸነፉ የታችኛውን ምክር ቤት ይቆጣጠራሉ።

አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜና በፔንሲልቬኒያ ለሴኔት የተወዳደሩት የዲሞክራቱ ዕጩ ጆን ፌተርማን ማሸነፋቸውን ይፋ አድርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስከአሁን ባለው ውጤት ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል። በፍሎሪዳ ማሪ ላ ጎ ቤታቸው ከቅርብ ሰዎቻቸው ጋር በመሆን “ምሽቱ ድንቅ ሆኖልናል” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።

አሜሪካኖች በዚህ ደረጃ በሁለት ጎራ ተሰልፈው አያውቁም እስኪባል ድረስ በዲሞክራቶችና በሪፐብሊካኖች መካከል ከፍተኛ የፖለቲካ ትንቅንቅ ተስተውሏል።

ሪፐብሊካኖች አሜሪካ የስደተኞች መፈንጫ ሆናለች፣ ኢኮኖሚው ላሽቋል፣ ወንጀል በርክቷል ዲሞክራቶች አገሪቱን አደቀቋት ሲሉ ይከሳሉ።

ዲሞክራቶች በበኩላቸው ዶናልድ ትራምፕ እና መሰሎቻቸው ኮንግረስን ከተቆጣጠሩ የአሜሪካ ዲሞክራሲ ውሃ ይበላዋል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

አሁን አሜሪካዊያን ውጤታቸውን በጉጉት እየጠበቁ የሚገኙባቸው አምስት ወሳኝ ግዛቶች አሉ።

እነዚህ አምስት ግዛቶች ውጤታቸው በቀጣይ ማን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን መቀመጫ ይቆጣጠራል የሚለውን የሚወስኑ ይሆናሉ።

እነዚህም ነቫዳ፣አሪዞና፥ ዊስኮንስን፥ ጆርጂያና አላስካ ናቸው።

ዲሞክራቶች ለምሳሌ በጆርጂያ ቢሸነፉ ነቫዳና አሪዞና ግዛትን ማሸነፍ አለባቸው። አለበለዚያ የሴኔትን ቁጥጥር ያጣሉ።

በነቫዳ ግዛት እስከዚህች ደቂቃ ድረስ ዲሞክራትና ሪፐብሊካን ከፍ ያለ ፉክክር ላይ ናቸው።

ነባሯ የዲሞክራቲክ ወኪል ካትሪን ኮርቴዝ ማትሮ ከሪፐብሊካኑ አዳም ሌክዛልት ጋር ተፋጠው ይገኛሉ። ቆጠራው በሂደት ላይ ነው።

ዲሞክራቶች ኔቫዳን ወይም አሪዞና ግዛትን ቢሸነፉ የግድ ዊስኮንሰንን ማሸነፍ ይኖርባቸዋል።

ሪፐብሊካኖች የታችኛውን ምክር ቤት እንደተፈራው ከተቆጣጠሩት ጆ ባይደን አዲስ ሕግና ፖሊሲን ለማስፈጸም እጅግ ይቸገራሉ።

ይህ በእንዲህ እያለ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት የረዥም ዘመን አፈ ጉባኤ የሆኑት ናንሲ ፒሎሲ ለ17ኛ ጊዜ ድጋሚ የተመረጡ ሲሆን ምናልባት ምክር ቤቱን ሪፐብሊካኖች ከተቆጣጠሩት አፈ ጉባኤነታቸውን ያጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።