ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ቻይና በካናዳ ፖለቲካ ጣልቃ እየገባች ነው ሲሉ ከሰሱ

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ
ታትሟል

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በአገራቸው ምርጫ ውስጥ ቻይና ጣልቃ ለመግባት ሙከራ አድርጋለች ሲሉ ከሰሱ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዲሞክራሲ ላይ “አደገኛ ጨዋታ” በመጫወት እና የካናዳ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ቤይጂንግን ከሰዋል።

የካናዳ መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም በቅርብ በተካሄዱ ምርጫዎች የተሳተፉ እና በቻይና የተደገፉ ዕጩዎችን ለይቷል የሚሉ ዘገባዎችን አውጥተው ነበር።  

የአገሪቱ ባለሥልጣናት እአአ 2019 ተካሂዶ በነበረው የፌደራል ምርጫ ቢያንስ 11 ዕጩዎች በቻይና ሲደገፉ እንደነበረ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ግሎባል ኒውስ የተሰኘው የካናዳ መገናኛ ብዙኃን በስም ያልጠቀሳቸውን ምንጮች ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ የቻይና ቅጥረኛ የሆኑ ግለሰቦች የምርጫ ቅስቀሳ አማካሪ ሆነው ለሰሩላቸው ዕጩዎች ቤይጂንግ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች።

ቶሮንቶ በሚገኘው የቻይና ቆንስላ የሚመራው ኦፕሬሽን የምክር ቤት አባላት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች አስርጎ በማስገባት በሚወጡ ፖሊሲዎች ላይ ጫና ለመፍጠር ተሰርቷል ብሏል መገናኛ ብዙኃኑ።

ጉዳዩን ተከትሎ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በካናዳ የውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮች የመግባት ቤይጂንግ “ፍላጎት የላትም” ብሏል።

ቻይና ጫና ለመፍጠር ከሞከረችባቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባል የሆኑበት ሊብራል ፓርቲ እና ተቃዋሚ ወግ አጥባዊ ፓርቲ ይገኝበታል ተብሏል። ይሁን እንጂ ይህ የቤይጂንግ ጥረት ምን ያህል እንደተሳካ የሚታወቅ ነገር የለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“የምርጫ ሂደታችንን እና ሥርዓታችንን ለማጠናከር እና ታዓማኒነቱን ለማረጋገጥ ጠንካራ እርምጃዎችን ስንወስድ ቆይተናል፤ በምርጫ ጣልቃ ገብነበትን ለመከላከል ሃብት ወጪ ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ።

“ቻይናም ትሁን ሌሎች በመላው ዓለም የሚገኙ አገራት በተቋማት እና በዲሞክራሲያችን ላይ አደገኛ ጨዋታ እየተጫወቱ ነው” ብለዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛህዎ ሊጂአን ቻይና በካናዳ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የላትም ብለዋል።

“አንድ አገር ከሌላው አገር ጋር ግንኙነቱን ሊገነባ የሚችለው እርስ በእርሱ ሲከባበር እና የጋራ ተጠቃሚነት ሲኖር ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ሰሜን አሜሪካዊቷ አገር “የካናዳ እና ቻይና ግንኙነትን የሚጎዳ አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ አለባት” ብለዋል።

ቻይና በካናዳ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ እየገባች ነው የሚለው ሪፖርት የወጣው የካናዳ ባለሥልጣናት ቻይና በካናዳ ግዛት ውስጥ ይፋዊ ያልሆነ “ፖሊስ” ጣቢያዎችን ከፍታለች የሚሉ ክሶችን እየመረመርን ነው ካሉ በኋላ ነው።

ባለፈው ወር የካናዳ ፖሊስ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ሪፖርት እንደተደረገው ሁሉ በካናዳ “ከፖሊስ ጣቢያዎች ጋር የተያያዙ የወንጀል ድርጊቶች” እየመረመርኩ ነው ብሎ ነበር።

አየርላንድ እና ኔዘርላንድስን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ቻይና የከፈተችው ሕገ-ወጥ ፖሊስ ጣቢያዎች ይዘጉልን ሲሉ ለቤይጂንግ ጥያቄ አቅርበው ነበር።

ቻይና በሌሎች አገራት ግዛት ውስጥ ከፍታቸዋለች የተባሉት ፖሊስ ጣቢያዎች የቤይጂንግ አስተዳደርን የሚተቹ ሰዎች ወደ ቻይና ተመልሰው የወንጀል ክሶች እንዲመሰረትባቸው ጫና የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል።