አሜሪካ በሕገ-ወጥ መንገድ የበረራ ቴክኖሎጂ ወደ ሩሲያ ልከዋል ያለቻቸውን ሁለት ግለሰቦች አሠረች

ታትሟል

በዩናይትድ ስቴትስ ካንሳስ ግዛት ሁለት ግለሰቦች በሕገ-ወጥ መንገድ የበረራ ቴክኖሎጂ ወደ ሩሲያ ልከዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የ59 ዓመቱ ሲሪል ግሪጎሪ ቡያኖእቨስኪ እና የ55 ዓመቱ ዳግላስ ሮበርትሰን አንድ የንግድ ኩባንያ አላቸው።

የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር እንደሚለው ሁለቱ ግለሰቦች በጣም ውስብስብ የሆነ የበረራ ቴክኖሎጂ ከሕግ እውቅና ውጭ ወደ ሩሲያ ለመላክ አሲረዋል።

ግለሰቦቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ያለፈቃድ የቴክኖሊጂ ውጤቱን ወደ ውጭ በመላካቸው እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እሥር ይጠብቃቸዋል።

ግለሰቦቹ ከዚህ በተጨማሪ ወንጀል ለመፈፀም በማሴር፣ ሐሰተኛ ማስረጃ በመያዝና ከአሜሪካ ሕግ ውጭ ዕቃ በማጋዝ ተከሰዋል።

ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ሁለቱ ሰዎች በፈረንጆቹ ከ2020 ጀምሮ የአሜሪካን የውጭ ንግድ ሕግ ሲጥሱ ቆይተዋል።

ተከሳሾቹ የሚልኩትን ዕቃ መዳረሻ ሃገር በመቀየር አጭበርብረዋል ይላል ዐቃቤ ሕግ።

የፍትሕ ሚኒስቴር እንደሚለው ከኅዳር 2020 እስከ የካቲት 2021 ባለው ጊዜ ከሩሲያ የበረራ ቴክኖሎጂ ተቀብለዋል።

አልፎም የሩሲያ የስለላ መሥሪያ ቤት አርማ ያለበት አንድ የኮምፒውተር ‘ፕሮሰሰር’ ተቀብለዋል ይላል።

ሲሪልና ዳግላስ የተባሉት ተከሳሾች ሕገ-ወጥ የውጭ ንግድ ወረቀት በመጠቀም የሚልኩትን ዕቃ መዳረሻ ጀመርን አደርገውታል ይላል የክስ መዝገባቸው።

ግለሰቦቹ በአርሜኒያና ቆጵሮስ በኩል የበረራ ቁሳቁሶችን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሩሲያ መላካቸውንም ክሳቸው ያሳያል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ያቋቋመው አዲስ ክፍል ነው የግለሰቦቹን ክስ እየተመለከተ ያለው።