ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ በዩክሬን ግዛት የሾመቻቸው ከፍተኛ ባለስልጣን በመኪና አደጋ ሞቱ
ሩሲያ በዩክሬን ኬርሶን ግዛት የሾመቻቸው ምክትል አስተዳዳሪ በመኪና አደጋ መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናትና ሚዲያዎች አስታወቁ።
የ45 አመቱ ክሪል ስትሬሞሶቭ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ከሁለት ወራት በኋላ ነበር የተሾሙት።
የዩክሬን ዜጋ የሆኑት ክሪል በአገራቸው ፖሊስ በአገር ክህደት ወንጀል ይፈለጉ ነበር።
በሩሲያ የኬርሶን አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ቭላድሚር ሳልዶ ምክትላቸው መገደላቸውን ገልጸው ሟቹ ባለስልጣን አምስት ልጆች እንዳሏቸውና ባለቤታቸውም ነፍሰጡር እንደነበረች ተናግረዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሞት በኋላ የሚሰጠውን የመንግሥት ሜዳሊያ እንዲሸለሙ አዋጅ አውጥተዋል።
ኢንተርፋክስ የዜና ኤጀንሲ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው የመኪናው አደጋ የደረሰው በኬርሶን ከተማ እና በደቡባዊ ምስራቅ ሩሲያ በምትገኘው ክሬሚያ ውስጥ በምትገኘው በአርማንስክ ከተማ መካከል ባለው መንገድ ላይ ነው።
በአጎራባቿ ዛፖሪዝሂሂያ ግዛት በሩስያ የተሾሙት ባለስልጣን ቭላድሚር ሮጎቭ እንደተናገሩት አደጋው የደረሰው በአደገኛ ሁኔታ ሊቀድማቸው የነበረውን የጭነት መኪና ለማስወገድ በሚሞክሩበት ወቅት ነው።
"ከእንደዚህ አይነት አደጋ የመትረፍ እድል አልነበራቸውም” ሲሉም አደጋ የደረሰበትን መኪና መንገድ ዳር ላይ ሆኖ የሚያሳይ ፎቶ በቴሌግራም ገጻቸው አጋርተዋል።
“ የክሪል መታጣት ለሁላችንም ትልቅ ኪሳራ ነው” ብለዋል።
የክሪል ስትሬሞሶቭ መሞታቸውን ከተዘገበ ከሰዓታት በኋላ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ሰርጌይ ሾይጉ የሩሲያ ወታደሮች ከምዕራባዊው የዲኒፕሮ ወንዝ ዳርቻ እንዲለቁ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። በዚህም ውሳኔ መሰረት ወታደሮቻቸው ቁልፍ ከሆነችው የሩሲያ ኬርሶን ይወጣሉ ማለት ነው።
ሩሲያ በዩክሬን ያደረገቸውን ወረራ ተከትሎ ከተቆጣጠረቻቸው ክልላዊ ማዕከላት መካከል የኬርሶን ግዛት ዋነኛው ነው።
ህይወታቸው ያለፈው ምክትል አስተዳዳሪ ከጦር ግንባሮች ላይ በየቀኑ ለኬርሶን በሚያስተላልፉት ዕለታዊ መግለጫ ታዋቂነትን አትርፈው ነበር።