የደቡብ ሱዳን የምክትል ፕሬዝዳንት የሬክ ማቻር መኖሪያ ቤትን ከበው የነበሩት የፀጥታ ኃይሎች እንዲነሱ ተደረገ

የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝድንት ሪክ ማቻር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝድንት ሪክ ማቻር
ታትሟል

በዋና ከተማዋ ጁባ ውስጥ የሚገኘውን የምክትል ፕሬዝዳንት ሬክ ማቻርን መኖሪያ ቤትን ከበው የነበሩት የደቡብ ሱዳን መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከአካባቢው መልቀቃቸው ተገለጸ።

የምክትል ፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ለቢቢሰ እንዳረጋገጠው ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ በሬክ ማቻር መኖሪያ ቤት ዙሪያ ተሰማርተው የነበሩት ኃይሎች ተነስተዋል።

የምክትል ፕሬዝዳንቱ የፕሬስ ክፍል ኃላፊ ፖክ ቦዝ ባሉዋንግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ማቻር ዛሬ ሰኞ ወደ ጽህፈት ቤታቸው ገብተው መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው።

የምክትል ፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ከሰዓት በኋላ መግለጫ ያወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

የፀጥታ ኃይሎቹ የማቻርን ቤት የከበቡት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ይፋ ያደረጉትን የአገሪቱ ብሔራዊ ጦር የሚመሰረትበትን መመሪያን የሚቃወም መግለጫ ካወጡ በኋላ ነው።

ከአራት ዓመት በፊት ሁለቱ ተቀናቃኝ መሪዎች ከሰላም ስምምነት ላይ ሲደርሱ ከተስማሙባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ብሔራዊ ሠራዊት መመስረት አንዱ ነበር።

ነገር ግን ማቻር በሰላም ስምምነቱ ላይ እንደሰፈረው ፕሬዝዳንት ኪር በጦር ሠራዊቱ እና በፖሊስ ኃይሉ ውስጥ ያሉ ሥልጣኖችን በእኩል እያጋሩ አይደለም ሲሉ ከሰዋል።

ጨምረውም ፕሬዝዳንቱ እየወሰዱት ያለው የተናጠል እርምጃ ከሰላም ስምምነቱ ተቃራኒ እና እየተካሄደ ያለውን ድርድር በግልጽ የሚቃወም ነው ብለዋል።

የምክትል ፕሬዝዳንቱን ክስ በተመለከተ የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ጽህፈት ቤት ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።

የሪክ ማቻር መኖሪያ ቤት በአገሪቱ ጦር መከበብ በአገሪቱ የተደረሰውን የሠላም ስምምነት እንዳያደናቅፍ ስጋት አሳድሯል።

የደቡብ ሱዳን ልዩ ኃይሎች የምክትል ፕሬዝዳንቱን መኖሪያ ቤት የከበቡት፤ ማቻር ከጥቂት ቀናት በፊት የመንግሥት ወታደሮች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሰዋል ብለው ቅሬታ ካሰሙ በኋላ ነው።

ጦሩ የምክትል ፕሬዝደንቱን መኖሪያ ቤት ለምን እንደከበበው ይፋ አላደረገም።

በአሁኑ ወቅት በማቻር እና በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ ቀጥሏል።

ማቻር ባለፈው ሳምንት በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር በሚገኙት በዩኒቲ እና በላይኛው ናይል ግዛቶች በመንግሥት ጥቃት እንደተፈጸመ አስታውቀው ነበር።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሁለቱ ወገኖች መካከል እስከ ጦር መማዘዝ የደረስ ግጭት ተከስቷል።

ተቃዋሚው የአገሪቱን የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያበቃ ያገዘውን የ2018 የሰላም ስምምነት ለማክበር መንግሥት ፍላጎት እንደሌለው በመግለጽ ከስምምነቱ መውጣቱን አስታውቋል።

የስምምነቱ ተፈጻሚነት ከታቀደለት ጊዜ ቢዘገይም አገሪቱን ወደ ሠላም ይመልሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ከሆነ ደቡብ ሱዳን በስድስት ዓመቱ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ ወደ ጎረቤት አገራት ተፈናቅለዋል።

ይህም በአፍሪካ ትልቁ የስደተኞች ቀውስ ነው ሲል ገልጾታል።