ኤርትራዊው የጌንት-ዌል የብስክሌት ውድድር በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢንያም ግርማይ በቤልጂየም የሚካሄደውን የጌንት-ዌል የብስክሌት የዕለት ውድድር በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ።
ቢንያም ግርማይ እሑድ በተካሄደው የጌንት-ዌል የብስክሌት ውድድር የዕለቱ አሸናፊ በመሆን ታሪክ ሠርቷል።
ማሸነፉን ተከትሎ በሰጠው ቃለ ምልልስ "የማይታመንና የሚገርም ነው። ይህን አልጠበቅኩም ነበር" ብሏል የ21 ዓመቱ ኤርትራዊ።
"አርብ ነበር ዕቅዴን የቀየርነው። የመጣነው ለጥሩ ውጤት ነው። ውድድሩ አስደናቂና የማይታመን ነው" ብሏል ቢንያም።
ቢንያም 30 ኪሎ ሜትር ሲቀር መምራት ከጀመሩት አራት ብስክሌተኞች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን፤ የውድድሩ መጠናቀቂያ 250 ሜትር ርቀት ሲቀረው አፈትልኮ በመውጣትም ማሸነፍ ችሏል።
የኢንተርማርቼ-ዋንቲ ጎበርት ጋላቢው ቢኒያም ግርማይ "ድሉ በተለይም ለአፍሪካውያን ብስክሌተኞች ትልቅ ለውጥ ያመጣል" ሲል ሃሳቡን ገልጿል።
የጃምቦ ቪስማው ብስክሌተኛ ክሪስቶፍ ላፖርት እስከመጨረሻው ከቢኒያም ጋር ቢታገልም ፈረንሳዊው ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
248.8 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የጌንት-ዌል በሚቀጥለው ሳምንት ለሚጀመረው እና ቱር ኦፍ ፍላንደርስ ለሚባለው የቤልጂየም ትልቁ ውድድር እንደመዘጋጃ ይቆጠራል።
በድንጋይ ንጣፍ፣ ኮብል መንገድ፣ ላይ የመጀመሪያ ውድድሩን ያደረገው ቢኒያም "በኮብል ላይ ተቸግሬ ነበር። አልተመቸኝም ነበር" ብሏል።
"መጨረሻ ላይ ሌሎቹ ጠንካሮች እንደሆኑ ባውቅም በራስ የመተማመን ስሜት ተሰማኝ።"
ቢንያም በፍላንደርስ ለመሳተፍ አልተመዘገበም።
የሴቶቹን ውድድር በጎዳና ውድድር ሻምፒዮን የሆነችው የትሬክ-ሴጋፍሬዶዋ ኤሊሳ ባልሳሞ አሸንፋለች።
ኮሎምቢያዊው ሰርጂዮ ሂጉይታ የቮልታ ሲክሊስታን ካታሎንያ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። ኢኳዶራዊው ሪቻርድ ካራፓዝ በሁለተኝነት አጠናቋል።
ሂጉይታ አንድ ሳምንት የፈጀውን ውድድር ከካራፓዝ በ16 ሰከንዶች ቀድሞ አጠናቋል። ፖርቹጋላዊው ጆአዎ አልሜዳ ደግሞ ሦስተኛ ሆኗል።












