በሔይቲ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የስደተኞች እንግልት አስቆጥቷቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ

ታትሟል

በሔይቲ ጉዳዮች የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ጎምቱው ዲፕሎማት ዳንኤል ፉተ የአገራቸው አሜሪካ የሔይቲያዊያን ስደተኞች አያያዝ ኢሰብአዊነቱን በመቃወም ሥልጣን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡

የመንግሥት መርጋት በሌለባትና ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ከተፈጥሮ ምስቅልቅሎሽ ጋር ተዳምሮ ለመኖር አስቸጋሪ አገር ካደረጋት ሔይቲ የተፈናቀሉ ስደተኞች ወደመጡበት መመለስ ኢሰብአዊነት ነው ያሉት ልዩ መልእክተኛው፤ አገሬ አሜሪካ የሔይቲ ስደተኞችን የምታንገላታበት መንገድ አግባብ ባለመሆኑ ሥልጣን ለቅቂያለሁ ብለዋል፡፡

የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ያስገቡት ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ከቴክሳስ ድንበር በርካታ የሔይቲ ስደተኞችን አሰናብታለች፡፡

ከቴክሳስ ድንበር በሺህ የሚቆጠሩ የሔይቲ ስደተኞች ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲሞክሩ ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ወደ ዐሥራ ሦስት ሺህ ስደተኞቹ በቴክሳስ ድንበር አቅራቢያ ድንኳን ቀልሰው ሙቀቱ 37 ዲግሪ በሚሆን በረሃ በአስቸጋሪ ሁኔታ እየኖሩ ይገኛሉ፡፡

ካለፈው እሑድ ምላሽ ብቻ በትንሹ 1ሺህ አራት መቶ ሔይቲያዊያን ወደየት እንደሚወሰዱ ሳይነገራቸው ከአሜሪካ በአውሮፕላን ተጭነው ወደ አገራቸው ተወስደዋል፡፡

አንዳንዶች ወደ ሔይቲ መመለሳቸውን በመቃወም ተመልሰው ወደ አውሮፕላኑ ለመግባት ሲተናነቁ ታይተዋል፡፡

በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው ዲፕሎማት ዳንኤል እንዳሉት ሔይቲ መንግሥት ያልጸናባት አገር ናት፡፡ ወደዚያች እየፈራረሰች ያለች አገር ሰዎችን አስገደዶ መላክ ሰብአዊነት አይደለም ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በርካታ ሚዲያዎች የአሜሪካ ፈረሰኛ የድንበር ጠባቂዎች የሔይቲ ስደተኞችን እየገረፉ ሲያባርሩ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ካጋለጡ በኋላ በባይደን አስተዳደር ላይ ጫናው በርትቷል፡፡

በርካታ ሔይቲያዊያን ወደ ስደት የወጡት በፈረንጆቹ በ2010 አገራቸው በከፍተኛ ርዕደ መሬት ከፈራረሰች በኋላ ነው፡፡

በዚህ ዓመት ደግሞ ፕሬዝዳንቷ ጆቨነል ሞይስ በሰው እጅ መገደላቸውን ተከትሎ አገሪቱ መረጋጋት ይበልጥ ርቋታል፡፡