ተኳርፈው የነበሩት ፈረንሳይና አሜሪካ ሰላም አወረዱ

ታትሟል

ፈረንሳይና አሜሪካ ሻክሮ የነበረውን ግንኙነታቸውን ዳግም ወደነበረበት ለመመለስ እየሠሩ ነው፡፡

በሁለቱ ወዳጅ አገራት መሀል ንፋስ የገባው የአውከስ ስምምነት በአሜሪካ፣ በዩኬና በአውስትራሊያ መካከል ከተፈረመ በኋላ ነው፡፡

ስምምነቱ ሦስቱን አገራት በኒክሊየር ኃይል የሚታገዝ የባሕር ሰርጓጅ መርከብ ቴክኖሎጂ ልውውጥ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው፡፡

ፈረንሳይ ስለዚህ ስምምነት ቀደም ብሎ ሊነገረኝ ይገባ ነበር፣ ወዳጃችሁ ብሆንም አግልላችሁኛል በሚል ከፍተኛ ቅሬታዋን አሰምታለች፡፡

ይህን የባሕር ሰርጓጅ መርከብ ውስብስብ ቴክኖሎጂን ለአውስትራሊያ ልታቀርብ ተስማምታ የነበረችው ፈረንሳይ ነበረች፡፡

ለዚህ አገልግሎትም የ37 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ክፍያ ስምምነት አድርጋ ነበር፡፡

ሆኖም ባልተጠበቀ ሁኔታ አውስትራሊያ ይህን ስምምነት ቸል በማለት ፊቷን ወደ አሜሪካ ማዞሯ ፈረንሳይን ክፉኛ አስቆጥቷታል፡፡

ፈረንሳይ እንደምትለው አውስትራሊያ ፊቷን ወደ አሜሪካ ማዞሯን የሰማችው ነገሩ ለሚዲያ ከመገለጹ ከአንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ነው፡፡

ፈረንሳይ ድርጊቱን ‹ከጀርባ በስለት መወጋት ነው› ስትል የህመሙን ኃያልነት፣ የክህደቱን ጥልቀት ገልጣ ነበር፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን አምባሳደሮቿን ከአሜሪካና በአውስትራሊያ እስከማስጠራት የደረሰ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ከባድ የሚባል እርምጃንም ወስዳ ነበር፡፡

ሆኖም ትናንት ኢማኑኤል ማክሮንና ጆ ባይደን ለግማሽ ሰዓት ያህል በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ነገሮች እየረገቡ ይመስላሉ፡፡

ፈረንሳይ አምባሳደሯን ወደ ዋሺንግተን እንደሚመለሱ የገለጸች ሲሆን ሁለቱ መሪዎች ደግሞ በዚህ ወር መጨረሻ በአውሮጳ አካል ለ አካል እንደሚገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

ሆኖም ከአውስትራሊያ የተመለሱት አምባሳደሯ ወደ ካንቤራ ስለመመለስ አለመመለሳቸው የተባለ ነገር የለም፡፡

የአውከስ ስምምነት በዋናነት በደቡባዊ ቻይና ባሕር የቻይናን ወታደራዊ ተጽእኖ ለመቋቋም የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡

ይህ ስምምነት ከ2ኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ወሳኝ ወታደራዊ ጥምረት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በዓለም ላይ በኑክሊየር የሚደግ ሰርጓጅ መርከብ ያላቸው አገራት ቻይናን ጨምሮ ሰባት ብቻ ናቸው፡፡