ቻይናዊው አባት በሁለት ዓመቱ የተሰረቀውን ልጃቸውን ከ24 ዓመታት በኋላ አገኙ

ታትሟል

ቻይናዊው አባት ጉዎ ጋንጋታ ለ24 ዓመታት ጠፍቶባቸው የነበረው ልጃቸውን አግኝተዋል።

ልጃቸው በሁለት ዓመቱ ነበር በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች የተጠለፈው። አባትየው ልጃቸውን ለማግኘት በመላው ቻይና በሞተር ሳይክል 500,000 ኪሎ ሜትር ተጉዘዋል።

ሻንዶንግ ግዛት ከሚገኝ ቤታቸው ልጃቸው ከተሰረቀባቸው ጊዜ አንስቶ ጉዎ ለ24 ዓመታት ያልፈለጉበት ቦታ የለም።

እአአ 2015 ላይ የልጃቸውን ታሪክ የተመረኮዘ ፊልም ሆንግ ኮንግ ውስጥ ተሠርቷል።

ቻይና ውስጥ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች ይሰረቃሉ።

ፖሊሶች የጉዎን ልጅ ያገኙት የዘረ ምርመራ በማድረግ ነው። ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ግሎባል ታይምስ ዘግቧል።

ቻይና ኒውስ እንዳለው፤ ልጁን የሰረቁት ጥንዶች ሸጠውት ገንዘብ ማግኘት ነበር እቅዳቸው።

ልጁ በቤተሰቦቹ ቤት ግቢ ብቻውን እየተጫወተ ሳለ ታንግ የተባለች ሴት አፍና ወሰደችው። ፍቅረኛዋ ሁ አውቶብስ ጣቢያ እየጠበቃት ነበር።

ልጁን ሄናን ወደተባለ ግዛት ወስደውት ሸጡት። ፖሊስ የጉዎን ልጅ ያገኘውም በዚሁ ግዛት እየኖረ ሳለ ነው።

ጉዎ እና ባለቤታቸው ለ24 ዓመት የጠፋባቸውን ልጃቸውን ሲያገኙት አቅፈውት እያለቀሱ "ልጃችን ተመለሰልን" ብለዋል።

እናትየው "ልጄ መጣህልኝ" እያሉ አልቅሰዋል።

አባትየው ደግሞ "ልጃችን ስለተገኘ ከዚህ በኋላ ደስተኛ ሆነን እንኖራለን" ብለዋል።

ሎስት ኤንድ ላቭ የተሰኘውና በልጁ መጥፋት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ፊልም ላይ አባትየውን ወክሎ የሚተውነው ላውም ቤተሰቡን እንኳን ደስ አላችሁ ብሏል።

"ወንድሜ ጉዎ ጽናትህን አደንቃለሁ" ማለቱም ተነግሯል።

እአአ በ1997 ልጃቸው የተሰረቀባቸው አባት ከ20 በላይ የቻይና ግዛቶችን ተዘዋውረው ፈልገውታል።

በዚህ ጉዞ የመኪና አደጋ ደርሶባቸው አጥንታቸው ተሰብሯል፣ ሌቦች ዘርፈዋቸዋል፣ ሁለት ሞተር ሳይክል ከጥቅም ውጪ ሆኖባቸዋል።

በተለያዩ የቻይና ግዛቶች ሲዘዋወሩ የልጃቸው ፎቶ ያለበት ፖስተር ይዘው ነበር።

ለፍለጋው ሲሉ ሀብታቸውን በሙሉ አሟጠዋል። ሲደክማቸው ድልድይ ስር ይተኙ፣ ገንዘብ ሲጨርሱ ደግሞ ይለምኑ ነበር።

ቻይና ውስጥ የልጆች ስርቆት እና ዝውውር ለዓመታት የዘለቀ ችግር ነው።

2015 ላይ የወጣ አሀዝ እንደሚያሳየው በየዓመቱ 20,000 ልጆች ገደማ ይሰረቃሉ። ከእነዚህ ልጆች አብዛኞቹ እዛው ቻይና ውስጥ ወይም ውጪ አገር ለማደጎ ይሸጣሉ።

እስካሁን ድረስ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጠፉ ልጆች የት እንደደረሱ አልታወቀም።

ለፖሊስ የተለያዩ ወንጀሎችን ለመጠቆም የተሠራ መተግበሪያ የፊት ገጽ ላይ የሚገኘው የጠፉ ልጆች መጠቂሚያ ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎች ልጆች እንዲሰረቁ የሚያመቻቹት የቤተሰቡ ጎረቤቶች ወይም ዘመዶች ናቸው።

ከዚህ በፊት ተሰርቀው በአጎራባች ግዛት የጡብ ፋብሪካ ውስጥ እንዲሠሩ የተገደዱ ልጆች ጉዳይ ማኅበረሰቡን አስቆጥቷል።

ፖሊስ በዋነኛነት የሚጠቀመው የዘረ ምል ምርመራ በማድረግ ነው። ልጆቻቸው የጠፉባቸው ሰዎች ዘረ መላቸውን ለፖሊስ ይሰጣሉ። ከዚያም ልጆቻቸው እንደተሰረቁ አውቀው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ዘረ መል ከሰጡ ፖሊስ ወላጅና ልጅን ያገናኛል።

ነገር ግን ብዙ ልጆች መሰረቃቸውን ስለማያውቁ ይህ አሠራር እንቅፋት ገጥሞታል።

በርካታ ቤተቦች ልጆቻቸው በተሰረቁባት ቻይና፤ ጉዎ ከ24 ዓመታት በኋላ ለልጃቸው ጋር መገናኘታቸው ብዙዎችን ያስደሰተ፣ የብዙዎችን ልብ የሰበረም ነው።