ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የናይጄሪያ ጋዜጦች በፊት-ገጻቸው ተመሳሳይ ተቃውሞ አደረጉ
የናይጄሪያ ጋዜጦች በሀገሪቱ ያለውን የፕሬስ ነጻነት ያኮስሳሉ የሚሏቸውን ሁለት የሚዲያ ረቂቅ ህጎች ለመቃወም የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ ዘመቻ አካል የሆነ ተመሳሳይ የፊት-ገጽ በጋራ አሳትመዋል፡፡
"የመረጃ መታገድ" ከሚል ርዕስ ጎን ለጎን የአንድ ልጅ ምስል የሚታይ ሲሆን በአፉ ምትክ የእስር ቤት ብረት ዘንጎች ተተክተው ይታያሉ።
የናይጄሪያ ፕሬስ ካውንስል እና ናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮሚሽን ባወጡት ረቂቆች ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት "እውነተኛ እና ጥራት ያለው አገልግሎት የማያረጋግጡ" ከሆነ 12 ሺህ 100 ዶላር ቅጣት እንደሚኖር ተካቷል።
ረቂቆቹ ሕግ ከሆኑ የሚፈረደባቸው ሰዎች እስከ ሦስት ዓመት ሊታሰሩ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ባለፈው ወር የብሔራዊ ምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙሃን እና የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር አጂቦላ ባሲሩ ረቂቆቹን ተከላክለዋል።
'አንድ ሰው እንደ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን ያሉ የመገናኛ ብዙሃን እንቅስቃሴን መቆጣጠሩ ሚዲያዎችን እያገቱ ነው ማለት አይደለም" ብለዋል፡፡
የናይጄሪያ የጋዜጠኞች ህብረት፣ የናይጄሪያ የአርታኢዎች ማኅበር እና የናይጄሪያ የጋዜጣ ባለመብቶች ማህበር በበኩሉ ከማሻሻያዎቹ ጀርባ ያለው ትክክለኛ ምክንያት የሚያወጧቸወቸውን መረጃዎች መከታተል እና መቆጣጠር ነው ብሏል፡፡
"ህብረተሰቡን የማወቅ እና የመሰማት መብትንም ይጥሳል" ይላሉ፡፡
የመረጃ መጥፋት ዘመቻው ለሁለት ቀናት ይቆያል፡፡