ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ ኮሪያ በስፖርት ማዘውተሪያዎች ውስጥ ፈጠን ያሉ ሙዚቃዎች መጫወትን አገደች

ታትሟል

በደቡብ ኮሪያ የሰውነት ማጎልመሻ ማዕከላት ወይም በጂም ውስጥ የሚከፈቱ ሙዚቃዎች ለስለስ ያሉ እንዲሆኑ ደንብ ተላለፈ፡፡

ይህም የሆነው ፈጣን ምት ያላቸው ሙዚቃዎች ላብ እንዲፈጠር ስለሚያደርጉ፣ እንዲሁም ሰዎች ቶሎ ቶሎ እንዲተነፍሱ ምክንያት ስለሚሆኑ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ በዋናነት የኮቪድ ሥርጭትን ሊያስፋፋ ስለሚችል ለስላሳ ሙዚቃዎች ማጫወት በተዘዋዋሪ ኮቪድን ሊገታ ይችላሉ ተብሎ የተዘየደ መላ ነው ተብሏል፡፡

በዚህ መመርያ መሰረት 120 ቢት በደቂቃ እና ከዚያ በታች የሆነ ምት ያላቸው ሙዚቃዎች ናቸው ተገቢ የሚሆኑትና በሰውነት ማጎልመሻዎቹ ውስጥ መጫወት የሚችሉት፡፡

ተንቀሳቃሽ ያልሆነ የመሮጫ መም (ትሬድሚል) ደግሞ ቢበዛ በሰዓት 6 ኪሎ ሜትር ብቻ እንዲፈጥን እንዲደረግ ታዟል፡፡

የጤና ባለሞያዎች እንደሚሉት ይህ መመሪያ ተግባራዊ ሲደረግ በስፖርት ማጎልመሻ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አተነፋፈሳቸው ከልክ በላይ እንዳይሆን፣ ላባቸውም እንዳይንቆረቆር ያስችላል፡፡

ይህም የኮቪድ ስርጭትን ይቀንሳል ብለዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ ከትናንት በስቲያ እሑድ አንድ ሺህ አንድ መቶ አዳዲስ ሰዎች በኮቪድ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ድንጋጤ ተፈጥሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርብ ዕለት እንዳስጠነቀቁት አገሪቱ በኮቪድ ምክንያት ትልቅ ምስቅልቅል ውስጥ ገብታለች፡፡ ከዚህ በላይ ጭንቅ መሸከም አትችልም፡፡

በዚህም የተነሳ መመርያዎቹ በጥብቅ እንዲተገበሩ አዘዋል፡፡

በዚህ መመሪያ ይበልጥ ተጸእኖ የሚደርስባቸው የዙምባና የኤሮቢክስ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

እነዚህ የእንቅስቃሴ አይነቶች ፈጠን ያለ ሙዚቃን የሚሹ በመሆናቸው፡፡

በአዲሱ መመሪያ መሰረት ሰውነት ማጎልማሻ ማዕከላት ገብተው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያዘወትሩ ሁሉ ቢበዛ መቆየት የሚችሉት ለሁለት ሰዓታት ብቻ ሲሆን ገላቸውን መታጠብ የሚችሉት ደግሞ ቤታቸው ሄደው ነው፡፡

የጂም ባለቤቶች በበኩላቸው አዲሱ መመሪያ ግራ እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡ እንዴት ነው ለስላሳ ሙዚቃ ማጫወት ኮቪድን የሚከላከለው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ጨምረውም፣ በርካታ ሰዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ‹ጂም› ውስጥ በሚሰሩ ጊዜ በግል ድምጽ ማጫወቻ ነው ሙዚቃ የሚሰሙት፡፡

እነዚህ ሰዎች ታዲያ መንግሥት ያዘዘውን ለስላሳ ሙዚቃ እየሰሙ እንደሆነ መከታተል የሚችለውስ እንዴት ነው ሲሉ መሰረታዊ ጥያቄን አንስተዋል፡፡