ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና አእዋፋትን የሚያጠቃ በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ላይ አገኘች
አንድ የ41 ዓመት ቻይናዊ ጎልማሳ ኤች10ኤን3 (H10N3) በተባለ በሽታ የተያዘ የመጀመሪያው ሰው መሆኑ ተገለጸ።
ይህ የበሽታ አይነት (በርድ ፍሉ) ከዚህ ቀደም በአእዋፋት እንጂ ሰዎች ላይ ታይቶ አይታወቅም።
ግለሰቡ እንዴት በበሽታው እንደተያዘ ዝርዝር መረጃ አልወጣም። ህመሙ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ እንደማይተላለፍ ይታመናል።
በቻይና ጂአንግሱ ግዛት ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ባለፈው ሳምንት ነበር በሽታው የተገኘበት። አሁን ከበሽታው አገግሞ ከሆስፒታል ሊወጣ እንደሆነ ተገልጿል።
የተለያዩ አይነት የአእዋፋት ህመሞች ያሉ ሲሆን፤ ከዶሮ ወይም ከሌሎች አእዋፋት ጋር በቅርበት የሚሠሩ ሰዎች በበሽታ መያዛቸው ተዘግቦ ያውቃል።
በበሽታው ከተያዘው ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ህመሙ እንዳልተገኘባቸው ተገልጿል።
የቤጂንግ ብሔራዊ የጤና ተቋም እንዳለው፤ ግለሰቡ ሆስፒታል የገባው ሚያዝያ 28 ሲሆን፤ ኤች10ኤን3 እንዳለበት የተገለጸው ከአንድ ወር በኋላ ነው።
ግሎባል ታይምስ እንደዘገበው ተቋሙ "በዓለም ላይ ኤች10ኤን3 የያዘው ሰው ሪፖርት ተደርጎ አያውቅም። ከጫጩት ወደ ሰው በመተላለፍ የአሁኑ የተለየ አጋጣሚ ነው። በስፋት የመሰራጨቱ እድልም አነስተኛ ነው" ብሏል።
በሽታው በስፋት የመተላለፍ እድሉ ውስን እንደሆነም ተገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለሮይተርስ የዜና ወኪል "አሁን ላይ ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ የሚጠቁም ነገር የለም" ብሏል።
"አቪን ኢንፍሉዌንዛ በጫጩቶች መካከል እንደሚሰራጨው ሁሉ የሰው ልጆችም ሊያዙ ይችላሉ። ይህ የሚያሳየን የኢንፍሊዌንዛ ወረርሽኝ ስጋት መኖሩን ነው" ሲልም ድርጅቱ ማብራሪያ ሰጥቷል።
አሁን ላይ ኤች5ኤን8 (H5N8) የሚባል ዝርያ አዕዋፍትን እያጠቃ ይገኛል። በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ጫጩቶችን ገድሏል።
የካቲት ላይ ሩስያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ዝርያ በሰው ላይ እንዳገኘች አስታውቃ ነበር።
ከአእዋፋተ ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ የተሰራጨው እአአ ከ2016 እስከ 2017 ሲሆን፤ 300 ሰዎች ሞተዋል።