በዩኬ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮናቫይረስ ሰው ያልሞተባቸው ቀናት ተመዘገቡ

ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም ከመጋቢት ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፉት 28 ቀናት ውስጥ በተደረገ ምርመራ በኮቪድ ምክንያት ምንም ሰው አለመሞቱን አስታውቃለች።

በዚህም መሠረት ትናንት ማክሰኞ 3 ሺ 165 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ሰኞ ደግሞ 3 ሺ 383 ሰዎች ተይዘዋል ተብሎ ነበር። ባለፈው ሳምንት በአማካይ 2493 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ በሕንድ የታየው የኮሮናቫይረስ አይነት በዩናይትድ ኪንግደም መከሰቱን ተከትሎ በርካቶች ሲያዙ የነበረ ሲሆን በአገሪቱም ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሮ ነበር።

በመንግሥት መረጃ መሠረት በሳምንቱ መጨረሻ እና መጀመሪያ አካባቢ የሚመዘገቡ የሟቾች ቁጥር አነስተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሚካሄደው ቆጠራ ስለሚቀንስና በርካታ ባለሙያዎች እረፍት ላይ ስለሚሆኑ ነው።

የጤና ሚኒስትሩ ማት ሀንኮክ ከመጋቢት በኋላ ምንም ሞት ሳይመዘገብ ማደሩ ለመላው አገሪቱ ጥሩ ዜና እንደሆነና እሳቸውም ደስ እንዳላቸው ገልጸዋል።

አክለውም "ክትባቶቹ በትክክል እየሠሩ ነው። ክትባቶቹ እናንተን፣ በዙሪያችሁ ያሉትን እና የምትወዷቸውን ሰዎች ከቫይረሱ እየተከላከሉ ነው''ብለዋል።

"ነገር ግን ምንም እንኳን ይህ ጥሩ ዜና ቢሆንም ገና ቫይረሱን አላሸነፍነውም። አሁንም በየቀኑ የሚያዙ ሰዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እባካችሁ እጃችሁን እና ፊታችሁን ታጠቡ፣ በቤት ውስጥ ስትሆኑ ንጹህ አየር እንዲገባ በርና መስኮት ክፈቱ፣ እድሉን የምታገኙ ከሆነ ደግሞ ሁለቱንም ዙር ክትባቶች ተከተቡ'' ሲሉ ተደምጠዋል።

በሌላ በኩል የእንግሊዝ የማኅበረሰብ ጤና ዳይሬክተሯ ዶክተር ይቮን ዶይል በበኩላቸው፤ ምንም ሞት አለመመዝገቡ የሚያበረታታ ነው ካሉ በኋላ አሁንም ቢሆን ሰዎች ክትባቱን ሄደው እንዲወስዱ ጥሪያቸውም አቅርበዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች፣ በየቀኑ በቫይረሱ ምክንያት ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች እና በየቀኑ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ጥር ላይ ከነበረው አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

በተጨማሪም በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ አዋቂዎች መካከል አንድ ሦስተኛዎቹ ሁለቱንም ዙር ክትባት ወስደዋል። በዚህም መሠረት ከ25 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሁለት ዙር ክትባት የወሰዱ ሲሆን፤ ከ39 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የመጀመሪያ ዙር ክትባቱን አግኝተዋል።