ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ81 ዓመቱ ሽማግሌ ‹‹ባሪያ›› የሚለው የስማቸው ቅጽል እንዲነሳ በፍርድ ቤት አስወሰኑ
በሰሜን አፍሪካዊቷ ቱኒዚያ ሐምደን ዳሊ የሚባሉ የ81 ዓመት ሽማግሌ ታሪካዊ የሚባል ውሳኔ ተወስኖላቸዋል፤ በፍርድ ቤት፡፡
ውሳኔው ከስማቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በስማቸው ውስጥ ‹አቲቅ› የሚል ተቀጽላ ይገኛል፡፡ ነገሩ ተቀጽላም ሳይሆን የመሀል ስም ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡
አቲቅ ማለት ደግሞ አውዳዊ ትርጉሙ "ባሪያ"› ማለት ነው፡፡
በቱኒዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ የቆዳ ቀለማቸው ጠቆር ላሉ ዜጎች የሚሰጥ የመሐል ስም ነው፡፡ በዚህም መሰረት የሽማግሌው ስም ሐምደን አቲቅ ዳሊ ሆኖ ቆይቷል፡፡
አቲቅ የሚለው የመሀል ስም በተለይም በድሮ ዘመን ባሪያ ሆነው ከተሰቃዩ ሰዎች ዘር የተገኘ ሰውን ያመላክታል፡፡
አቲቅ የቃሉ ጥሬ ትርጉም ‹ከባሪያነት ነጻ የሆነ›› ማለት ቢሆንም በአመዛኙ የሚያያዘው ግን ከባሪያ ቤተሰብ የተገኘን ሰው በመሆኑ ለመገለልና ለመገፋት እንደ ልዩ መታወቂያ የሚታይ ነው፡፡
ቱኒዚያ የሕዝቧ 15 ከመቶ የሚሆኑት ጥቆር ቆዳ ያላቸው ዜጎች ናቸው፡፡
እኚህ አዛውንት ታዲያ ስማቸው ውስጥ አቲቅ የሚለው ቃል በመሰንቀሩ ምክንያት ሕይወታቸውን ሙሉ በገዛ አገራቸው ሲገፉ፣ እንደ 2ኛ ዜጋ ሲታዩና ሲንቋሸሹ ቆይተዋል፡፡
እንደርሳቸው ያሉ ከባሪያ ዘር የተገኙ ናቸው ተብለው የሚታሰቡና ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ቱኒዚያዊያን ሥራ ለማግኘትም ይቸገራሉ፡፡
‹አቲቅ የሚለው ቃል ከባሪያነት ነጻ የሆነ ማለት ቢሆንም በማኅበረሱ የሚሰጠው ትርጉም ግን ተቃራኒው ነው ይላሉ› የሽማግሌው ጠበቃ ሐነን ቢን ሐሴና ለሮይተርስ፡፡
በቱኒዚያ ታሪክ ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ታሪካዊ የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡
የቱኒዚያ 15 ከመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ከሰሀራ በታች ካሉ አገሮች የፈለሱና ድሮ በባሪያ ንግድ ወደ ቱኒዚያ የገቡ አፍሪካዊያን የልጅ ልጆች እንደሆኑ ይታመናል፡፡
ቱኒዚያ የባሪያ ንግድን ያቆመችው እንደ አውሮጳዊያኑ በ1846 ነው፡፡