ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሊቨርፑሉ ቨርጂል ቫንዳይክ ለወራት ከሜዳ ሊርቅ እንደሚችል ተገለጸ
ቫን ዳይክ ያጋጠመውን ጉዳት ተከትሎ ለወራት ኳስ ላይጫወት እንደሚችል ተገለጸ።
የሊቨርፑልና የኔዘርላንድስ የመሀል ተከላካዩ ቨርጂል ቫን ዳይክ ቅዳሜ ዕለት በፕሪምየር ሊጉ ከኤቨርተን ሁለት አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ምክንያት ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልገው ተገልጿል።
የ29 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ ከኤቨርተኑ ግብ ጠባቂ ጆርዳን ፒክፎርድ ጋር በመጋጨቱ ነበር በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ተቀይሮ የወጣው።
ጉልበቱ ላይ የሚደረግለት ቀዶ ህክምና ለምን ያክል ጊዜ ከእግር ኳስ ሜዳ እንደሚያርቀው ያልታወቀ ቢሆንም ከዚህ በፊት ከነበሩ ልምዶች አንጻር ለወራት ሊቆይ እንደሚችል ተገልጿል።
ቫንዳይክ በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፈው ምልዕክት ''ለአዲሱ ፈተናዬ ተዘጋጅቻለሁ። በአሁኑ ሰዓት እንዴት ማገገም እንዳለብኝ ብቻ ነው ማስብ የምፈልገው፤ በፍጥነት ወደ እግር ኳስ ለመመለስ የቻልኩትን በሙሉ አደርጋለሁ'' ብሏል።
አክሎም ''ምንም እንኳን የተፈጠረው ነገር ቢያሳዝንም ጠንካራ እምነት ያለኝ ሰው ነኝ። ሁሌም ቢሆን በከባድ ፈተና ውስጥ ትልቅ ዕድል አለ፤ ስለዚህ በፈጣሪ እርዳታ በተሻለ ብቃትና ጥንካሬ ኳስ መጫወት እጀምራለሁ'' ብሏል።
ምንም እንኳን ጉልበት ላይ ከሚደረግ ቀዶ ህክምና ለማገገም በርካታ ወራትን ሊፈጅ ቢችልም የቫንዳይክ ቡድን ሊቨርፑል ግን ተከላካዩ ለምን ያክል ጊዜ ከጨዋታ እንደሚርቅ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ቀዶ ህክምናውም ቢሆን አፋጣኝ አይደለም የተባለ ሲሆን ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችንም ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።
የቫንዳይክ ጉዳት ለአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ትልቅ ፈተና ነው። የእሱን ጉዳት ተከትሎም ፊታቸውን ብዙም ወደማያስተማምኑት ጆ ጎሜዝ እና ጆዌል ማቲፕ ማዞር ነው ያላቸው አማራጭ።
ጎሜዝ እና ማቲፕ እአአ ከ2017 በኋላ አንድ ላይ ተሰልፈው የማያውቁ ሲሆን ይህ በራሱ ሌላ ለክሎፕ ትልቅ ፈተና ይሆናል ተብሏል።
በርካቶችም ገና ከአሁኑ አዲሱ የውድድር ዓመት ለሊቨርፑል ከባድ ሊሆን እንደሚችል እየገለጹ ሲሆን የቫን ዳይክ አለመኖር የተከላካይ መስመሩን በእጅጉ እንደሚያሳሳው ተገምቷል።