ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኬንያ ዳግም የኮቪድ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ሰግታለች
ታትሟል
ኬንያ 2ኛ ዙር የኮቪድ ወረርሽኝ አስግቷታል፡፡
የኬንያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ማስጠንቀቂያ አውጥቷል፡፡ በአገሪቱ የኮቪድ ወረርሽኝ በድጋሚ ሊያንሰራራ ስለሚችል ዜጎች ከወዲሁ ጥንቃቄ ያድርጉ ብሏል፡፡
ሚኒስትሩ ሙታሂ ካግዌ እንዳሉት ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የእንቅስቃሴ ገደብ ማላላታቸውን ተከትሎ የኮቪድ ተያዦች ቁጥር ጨምሯል፡፡
የወረርሽኙ ምጣኔ በ12 ከመቶ የጨመረ ሲሆን ባለፈው ወር ግን 4 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ የጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ የኮቪድ ታማሚዎች ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡
‹‹ምንም ጥያቄ የለውም፤ በርካታ አዳዲስ ሰዎች በወረርሽኙ እየተጠቁ ነው፡፡ ወደ ዳግማዊ የወረርሽኝ ዘመን እያዘገምን እንደሆነ አትጠራጠሩ›› ብለዋል ሙታሂ ካግዌ፡፡
ሚኒስትሩ በዋናነት ችግር ብለው ያነሱት የዜጎች መዘናጋት ነው፡፡ የፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ የመሸታ ቤቶች መከፈት እና ዜጎች ጭምብል ለማጥለቅ ዳተኛ መሆናቸውን ነው፡፡
‹‹በድንገት አይደለም ወረርሽኙ የጨመረው፡፡ ልንደነቅ አይገባም፡፡ መመርያዎችን ቸል እያልንናቸው ስለሆነ ነው›› ብለዋል ሚኒስትሩ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡
ኬንያ በአሁኑ ሰዓት 45ሺ የሚሆኑ ዜጎች በኮሮና ተህዋሲ ተጠቅተውባታል፡፡ የሞቱባት 832 ሰዎች ናቸው፡፡