እስራኤልና ባሕሬይን የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሠረቱ

ታትሟል

እስራኤል ከከበቧት የመካከለኛው ምሥራቅ አረብ አገራት ጋር ግንኙነቷ እየሰመረላት ነው፡፡ ትልቁ ሚና ታዲያ የዶናልድ ትራምፕ ነው፡፡

እስራኤል አሁን ደግሞ 4ኛዋን የአረብ አገር ማሳመን ችላለች፡፡

እስራኤል ከባሕሬይን ጋር በዋና ከተማዋ ማናማ ትናትን እሑድ ስምምነት አድርጋለች፡፡

ብዙዎቹ የአረብ አገራት ለዐሥርታት እስራኤልን አግልለዋት ቆይተዋል፡፡ ዋናው ምክንያታቸው ደግሞ እኛ ለእስራኤል እውቅና የምንሰጠው ከፍልስጤም ጋር ሰላም ስታወርድ ብቻ ነው በሚል ነበር፡፡

አሁን ግን በዚህ አቋማቸው ለመጽናት አረብ አገራት ያሉበት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲሁም የአገራት አሰላለፍ የሚፈቅድ አልሆነም፡፡

ባሕሬይን ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ስታድስ ከአረብ አገራት የመጀመርያው አይደለችም፡፡

ከዚህ ቀደም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ በተለያየ ጊዜ የሰላምና የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል ተፈራርመዋል፡፡

ይህም እስራኤል አገር ከሆነችበት እንደ አውሮጳዊያኑ 1948 ወዲህ የተደረጉ ስምምነቶችን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡

ፍልስጤም ስምምነቱን ‹ወዳጅ በሚሉት ሰው ከጀርባ በጩቤ የመወጋት ያህል ነው› ብላለች፡፡

ከትናንቱ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ባሕረይንና እስራኤል አንዱ በሌላው አገር ኤምባሲዎቻቸውን እንደሚከፍት ይጠበቃል፡፡

የእስራኤል ሚዲያዎች እንደዘገቡት በሁለቱ አገራት ስምምነት ውስጥ አንድም ቦታ ላይ የፍልስጤሞች ጉዳይ አልተነሳም፡፡

ከፊርማው ሥነ ሥርዓት በኋላ የባሕሬይን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላጢፍ ቢን ራሺድ አልዛያኒ ባደረጉት ንግግር ስምምነቱ ሁሉን አቀፍ ትብብርን የሚመለከት በመሆኑ ፍሬያማ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

ወደ ባሕረይን ያቀናው የእስራኤል ልኡክ ጉዞውን ያደረገው በበረራ ቁጥሩን 973 ነው፡፡ በዚህ ቁጥር በረራው መሰየሙ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይህም የባሕሬይን የስልክ መለያ ቁጥር በመሆኑ ወዳጅነቱን ለማጠንከር ነበር፡፡

ልኡኩ በበራውንም ያደረገው በሳኡዲን የአየር ክልል በኩል ነው፡፡ ሳኡዲ እስከአሁን ከእስራኤል ጋር ወዳጅነትን በይፋ አላደሰችም፡፡ ሆኖም መሐመድ ቢን ሳልማን ይህንኑ ማድረጋቸው የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የሚቀር አይሆንም እየተባለ ነው፡፡

የሱኒው ሙስሊም ዓለም መሪ አድርጋ ራሷን የምትመለከተው ሳኡዲ ደመኛዋ አድርጋ የምትመለከታትን ኢራንን ለመደምሰስ ከእስራኤል ጋር ወዳጅነት ከመመሥረት ወደ ኋላ ትላለች ተብሎ አይታሰብም፡፡

የተባበሩት ኢምሬቶች፣ ባሕሬይን እና ሳኡዲ አረቢያ በይበልጥ ከእስራኤል ጋር ያወዳጃቸው የጋራ ጠላት ኢራን ብትሆንም በርካታ ሌሎች ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ምክንያቶች አሏቸው፡፡

በዋናነት ግን ኢራን በአካባቢው የሺአ ኢዝላምን ለማስፋፋት ትጥራለች፣ የበላይነት ከያዘችም ታጠፋናለች ብለው ይሰጋሉ፣ እነዚህ አገራት፡፡

የአሜሪካው የፋይናንስ ሹም ስቲቭ የእስራኤልን ልኡክ አጅበው ባሕሬይን የተገኙ ሲሆን ነገ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ይገባሉ፡፡

እስራኤል የፍልስጤም ሕጋዊ ግዛቶችን በኃይል የያዘች ሲሆን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን ጩኸት ቸል በማለት በዌስት ባንክ አዳዲስ ሰፈራቸውን እያስፋፋች ትገኛለች፡፡

በከፍተኛ የኑሮ ምስቅልቅልና ድህነት ውስጥ የተዘፈቁት ፍልስጤማዊያን ወዳጅ በሚሏቸው አገራት ገሸሽ መደረጋቸው ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮባቸዋል፡፡