ብራዚል ለሴት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከወንዶች እኩል መክፈል ጀመረች

የብራዚል የሴት ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የብራዚል ሴት ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጫዋቾች ከእንግዲህ ከወንድ እግር ኳስ ተጨዋቾች እኩል እንደሚከፈላቸው የብራዚል እግር ኳስ ማኅበር አስታወቀ።

ይህ ብቻም ሳይሆን ሁሉም ተጨዋቾች፣ ጉርሻ እና የሽልማት ገንዘብ እንዲሁም በልምምድ ላይ ሳሉ የሚሰጣቸው የኪስ ገንዘብ በሙሉ ከወንዶች ጋር እኩል እንዲሆን ተወስኗል።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሮጄሪዮ ካቦክሎ እንዳሉት ይህ ውሳኔ የተላለፈው ባለፈው መጋቢት ወር ነው።

ብራዚል የወሰችውን ዓይነት እርምጃ እንግሊዝም ከባለፈው ጥር ጀምሮ ተግባራዊ አድርጋለች።

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር ቃል አቀባይ እንዳሉት ሴቶች ከወንዶች እኩል ደመወዝም ሆነ ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ።

ብራዚል ለዓለም ዋንጫም ሆነ ለኦሎምፒክ ተወዳዳሪዎቿ በክፍያ ረገድ የጾታ መድልዎን አስቀርታለች።

እስካሁን አውስትራሊያ፣ ኖርዌይ እና ኒውዚላንድ ለሴት ተጨዋቾች ከወንዶች እኩል እንዲከፈላቸው ቀድመው የወሰኑት አገራት ናቸው።

የብራዚል የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከባለፈው መጋቢት ጀምሮ ምንም ዓይነት ውድድር አላደረገም። ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ እየተስፋፋ በመሄዱ ነው።

ብራዚል በተህዋሲው የተያዙ ዜጎቿ ቁጥር ከአሜሪካና ከሕንድ ቀጥሎ ከዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።