ልደት ፤ ወጣቱ ለልደቱ የተሰጠውን ውስኪ በመሸጥ የ40ሺህ ፖውንድ ቤት ሊገዛ ነው

ማቲው ሮብሰን ይባላል፡፡ አባቱ አንድ ነገር አስለምደውታል፡፡
በየዓመቱ ልደቱ ሲሆን 18 ዓመት ዕድሜ ያለው ውስኪ ገዝተው ይሰጡታል፡፡ ልጁ ውስኪውን ያጠራቅማል፡፡ አሁን 28 ዓመት ደርሷል፡፡
ሮብሰን የተወለደው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1992 ነው።
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አባቱ በድምሩ 5ሺህ ፓውንድ አውጥተዋል፡፡ በየዓመቱ አንድ ውስኪ ለልደቱ ለመግዛት፡፡ እስከዛሬ 28 የውስኪ ጠርሙሶችን ገዝተውለታል፡፡
የውስኪው ዓይነት ማካላን የሚባል ነው፡፡ አሁን ዋጋው ንሯል፡፡
አባትየው ለ28 ጠርሙስ ውስኪ በ28 ዓመታት ውስጥ በድምሩ 5ሺህ ፓውንድ ብቻ ያውጡ እንጂ አሁን ላይ ውስኪዎቸ እስከ 40ሺህ ፓውንድ ይሸጣሉ፡፡
ሮብሰን እንደሚለው ውስኪ ለልጅ ተገቢ የልደት ስጦታ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አባቴ ውስኪዎቹን በፍጹም እንዳልከፍታቸው ያስጠነቅቀኝ ስለነበር ለዚህ በቅቻለሁ ብሏል፡፡
የሮብሰን አባት ፒት ይባላሉ፡፡ ስኮትላንድ ነው የሚኖሩት፡፡ በ1974 የተመረተው ዊስኪ ለመጀመርያ ጊዜ የገዙለት እንዲሁ እንደዋዛ ነበር፡፡
"እንደቀልድ በየዓመቱ አንድ ውስኪ ብሰጠው 18 ዓመት ሲሆነው 18 ዊስኪ ይኖረዋል ብዬ አሰብኩ፡፡ ነገሩን ለማድመቅ ነው እንጂ ለልጄ የምሰጠው ስጦታ ግን ዊስኪ ብቻ አልነበረም" ብለዋል፡፡
አሁን ማካላን ዊስኪዎች ተፈላጊ ናቸው፡፡ እንደ ቅርስ የሚሰበሰቡ የዊስኪ አይነቶች ናቸው፡፡ የነበራቸው ዋጋም በጣም ጨምሯል፡፡
አሁን ዊስኪዎቹን ማርክ ሊትለር የተባለ እሳት የላሰ የዊስኪ ደላላ ሊሸጣቸው ነው፡፡ ምርጥ ስብስቦች ናቸው ብሏል ለቢቢሲ፡፡
ባለፉት ዓመታት የእነዚህ ውስኪዎቹ ዋጋ እጥፍ በእጥፍ ነው የጨመረው፡፡ ብናጣ ብናጣ እስከ 40ሺህ ፓውንድ እንሸጣቸዋለን ይላል፡፡
ዊስኪዎቹ የሚሸጡት ለኒውዮርክ ወይም ለእሲያ ገበያ ነው፡፡
ሮብሰን በ40ሺህ ፓውንዱ ቤት ለመግዛት እያሰበ ነው፡፡













