የቱኒዝያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣናቸው ለቀቁ

ታትሟል

የቱኒዝያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤልይስ ኤል ፋክህፋክህ ከስልጣናቸው ለቀቁ።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ቢሮ እንዳሳወቀው ርዕሰ ብሄሩ መልቀቂያቸውን በትናንትናው ዕለት አስገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገንዘብ ቅሌት ውስጥ ገብተዋል በሚለው ውንጀላ ከፓርላማ አባላት ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸውም ነበር ተብሏል።

በፓርላማው ውስጥ ለዘብተኛ የሙስሊም ፓርቲን ወክለው ኤናህዳና ሌሎችም የተወካይ አባላት ድምፃቸውን በመጠቀም ከስልጣን እንደሚያወርዷቸውም ከሰሞኑ እየተነገረ ነበር።

በቱኒዝያ የአስተዳደር ስርዓት ውስጥ ለስድስት ወር በመቆየት ለአጭር ጊዜ በስልጣን የቆዩ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነዋል።

ከስልጣን የወረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያዩ የግል ኩባንያዎች 15 ሚሊዮን ዶላር የሚገመተው ድርሻቸው በመንግሥት ስራዎች አላግባብ በሆነ መልኩ ውል አሸንፈዋል በሚልም ነው በሙስና የተወነጀሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስና ፈፅመዋል የሚለውን ክስ ከዚህ ቀደም ከመካድ በተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ ስህተት ከተገኘም ከስልጣን እወርዳለሁ ብለው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን መልቀቅ አስመልክቶም ከቢሯቸው የወጣው መግለጫ የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ያለመና ፕሬዚዳንቱም ከዚህ ቀውስ እንዲወጣ እድል የሰጠ ነው ብሏል።

ፕሬዚዳንቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተተኪ በሳምንት ውስጥ ይሾማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የሚሾሟቸውም ሰው በሁለት ወራት ውስጥ የፓርላማ አባላቱን ድምፅ ማግኘት ይኖርባቸዋል ተብሏል።