በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የመናገር ነፃነት አደጋ ላይ ነው- ሂዩማን ራይትስ ዎች

የፎቶው ባለመብት, hrw
የኢትዮጵያ መንግሥት የኮቪድ-19ን ለመከላከል ያስተላለፋቸው ገደቦችና ለአምስት ወራት የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመናገር ነፃነትን ለመገደብ እየተጠቀመበት ነው ሲል የሂዩማን ራይትስ ዎች ተቸ።
ድርጅቱ በመግለጫው ባለፈው ወር ጠበቃ ኤልሳቤጥ ከበደና ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ አስተያየት በመስጠታቸው መታሰራቸውን ጠቀሷል።
ሪፖርቱ እንዳለው ኮሮናቫይረስ በአገሪቱ እንዳይስፋፋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጠኞችንና መንግሥትን የሚተቹትን ለማሰር እየዋለ ነው።
"ስለቫይረሱ የሚሰራጩ የተሳሳተ መረጃዎች ስጋት ቢሆኑም የመናገር ነፃነትን ለመገደብ ግን ሰበብ ሊሆኑ አይገባም" ያሉት የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላይቲቲያ ባደር፣ መንግሥት ያየሰው ሽመልስ ላይ የከፈተውን ክስ ውድቅ ማድረግ፣ ኤልሳቤጥ ከበደንም ከእስር መልቀቅ አለበት እንዲሁም ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ስለገለፁ ብቻ ማሰር ማቆም ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮቪድ-19 ተያዘ ሰው ከተገኘ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል ይረዳል ያሉትን እርምጃ ያስተላለፉ ሲሆን በወቅቱ መገናኛ ብዙኀንም "ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ" እንዲያደርሱ አሳስበው ነበር።
ከዚህ በኋላም በትግራይ ቴሌቪዥን ጣብያ ፖለቲካዊ ፕሮግራሞች የሚያቀርበው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በግል የፌስ ቡክ ገፁ ላይ መንግሥት በኮቪድ-19 ምክንያት ለሚሞቱ ሰዎች 200 ሺህ ጉድጓዶች እንዲቆፈሩ አዝዟል ሲል ጽፏል።
በወቅቱ መንግሥት መረጃው ስህተት ነው ሲል አስተባብሏል።
በሚቀጥለው ቀን ጋዜጠኛው ለገጣፎ አካባቢ ከሚገኘው ቤቱ በፖሊስና በደህንነት ሰዎች ተይዞ መታሰሩ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በሚል ካሰረው በኋላ ለሶስት ሳምንት ክስ ሳይመሰርት እንዳቆየው የገለፀው መግለጫው፣ በኋላም በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ በዋስ እንዲለቀቅ ቢወሰንም የፌደራል ፖሊስ በመካከል ጣልቃ ገብቶ ይግባኝ በማለት ማሻሻያ የተደረገበትን የፀረ ሽብር ሕግ በመጣስ ከስሶታል ብሏል።
ለሁለተኛ ጊዜ የፌደራል ፍርድ ቤት ለጋዜጠኛ ያየሰው የዋስትና መብቱን አስጠብቆለት ሊለቀቅ መቻሉን መግለጫው አክሎ አስፍሯል።
የሂይማን ራይትስ ዎች እንዳለው ከሆነ ያየሰው የተከሰሰው በአዲሱ የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃ ሕግ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በጎ ፈቃደኛ ጠበቃ የሆነችው ኤልሳቤጥ በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት በቁጥጥር ስር መዋሏን ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።
ድርጅቱ ከምትሰራበት ተቋም አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ኤልሳቤጥ እስካሁን ድረስ ክስ ያልተመሰረተባት ሲሆን ነገር ግን " ግጭት የሚያነሳሳ" ሀሰተኛ መረጃ በፌስ ቡክ በማሰራጨት ተወንጅላለች ብሏል።


ግለሰቧ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል ያለቻቸውን ሰዎች በስም ጠቅሳ በፌስቡክ ገጿ ላይ መፃፏ ተገልጿል።
የክልሉ ባለሰልጣናት በቫይሱ ተይዘዋል ተብለው በስምና በብሔር የተጠቀሱ ሰዎችን እንዲሁም ከእነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች በአጠቃላይ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል። በበወቅቱ በግለሰቧ የተፃፈው መረጃ ተሰርዞ ማስተካከያ ተደርጎበታል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዲህ አይነት መረጃዎች ግለሰቦችን ደህንነት የሚጋፋ መሆኑን ገልጿል። የግለሰቦችንም የህክምና መረጃ ይፋ ማድረግ ለማግለልና መድልዖ ያጋልጣል ሲል አስፍሯል።
ነገር ግን እንዲህ አይነት ድርጊቶች በወንጀል መታየት የለባቸውም ሲል በመግለጫው ላይ አስቀምጧል።
በኢትዮጵያ የአስቸኴይ ጊዜ አዋጁ ከተደነገገ በኋላ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ህጉን የሚጥሱ ሰዎችን ያስጠነቀቁ ሲሆን ሐሰተኛ ዜናዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ሚዲያ ተቋማትንም አስጠንቅቀዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን ያሳለፈች ሲሆን በእነዚህ ወቅቶች በርካታ ሰዎች መታሰራቸው ይታወሳል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚደርሱ ጥሰቶችን ለመከላከል ገለልተኛ አካል ምልከታ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም የሚከታተል ቡድን ያቋቋመ ሲሆን የሰብኣዊ መብት ኮሚሽንና የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶችም ሊሳተፉ እንደሚገባ ድርጅቱ በመግለጫው ላይ አትቷል።
" የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የከዚህ ቀደሙን ስህተት እንዳይደግሙት" ያሉት ባደር " በቀጣዮቹ አምስት ወራት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ዜጎች በአዋጁ ወቅት የተጣሉ ድንጋጌዎችን በመጠቀም የመብት ጥሰት እንደዳይኖር ከዚያም በኋላ እንዳይቀጥል" ሊከታተሉ ይገባል ብለዋል።












