መኪና ለመግዛት የወላጆቹን መኪና እስነስቶ የሄደው የ5 ዓመት ህጻን ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Courtesy Utah Highway Patrol
አንዳንድ ህፃናት አጣፍጠው የሰሩላቸውን አልበላም ብለው ወላጆቻቸውን ያስቆጣሉ፤ ያስጨንቃሉ፤ የድመት ጭራ እየጎተቱ በመጫወት ራሳቸው ለአደጋ ይጋብዛሉ።
የአምስት ዓመቱ አንድርያን ግን የቤተሰቦቹን መኪና አስነስቶ ሲያሽከረክር ፖሊስ አስቁሞ በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ይህ የሆነው በአሜሪካ ዩታህ ግዛት ነው። ፖሊስ በዋና ጎዳና ላይ ዝግ ብሎ የሚሄድ መኪና ወዲያና ወዲህ ሲዋልል አስተዋለ። ከዚያም አሽከርከካሪው ጥጉን ይዞ እንዲያቆም ተጠየቀ። አሽከርካሪው የፖሊስን ትዕዛዝ አክብሮ አቆመ።
ፖሊስ ግን የተመለከተው እጅጉን እንዳስደነገጠው ተናግሯል።
ልጁ ወዴት እንደሆነ ሲጠየቅም ላምበርጊኒ ለመግዛት እየሄደ መሆኑን አስረድቷል።
ጉዳዩን የልጅ ነገር ብለው ንቀው የሚተዉት አልሆነም። ምክንያቱም ልጁ ከወላጅ እናቱ ጋር በዚሁ ጉዳይ እሰጥ አገባ ውስት ገብቶ ነበር ተብሏል።
እናቱን ይህንን ቅንጡ መኪና ግዢልኝ ሲል ፈትሮ ይዟት ነበር ተብሏል። የመኪናው ዋጋ ደግሞ አይቀመስም። ዝቅተኛው እንኳ 180ሺህ ዶላር ነው የተተመነው።
የዩታህ ፖሊስ መርምሬ ደረስኩበት እንዳለው የአምስት ዓመቱ ህፃን መኪና አስነስቶ ወደ ካሊፎርኒያ ለመሄድ የወሰነው ላምበርጊኒውን ገዝቶ ለመምጣት ነው።
አሁንስ የልጅ ነገር እንበል ይሆን?
እስቲ ምን ያህል ገንዘብ ይዞ ወደ ካሊፎርኒያ ጉዞ እንደጀመረ ፖሊስ ያለውን አናንብብ።
በአምስት ዓመቱ ህፃን ኪስ ውስጥ ሶስት ዶላር ተገኝቷል። ገንዘብ እንኳ ትንሽ ያጥረው ነበር ይላሉ ፖሊሶች።
ፖሊስ በአሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ ያገኘውን ማሙሽ ሲመለከት መጀመሪያ የአካል ጉዳተኛ መስሎኝ ነበር ብሏል፤ በኋላ ግን እድሜውን ሲጠይቅ 'ጉድ ሳይሰማና ሳይታይ መስከረም አይጠባም' ብለው ሳይተርቱ አልቀሩም።
ልጁ እድሜውን ሲጠየቅ አምስት አለ።
ይህ ልጅ መኪና የመግዣ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የማሽከርከሪያም እድሜ ያጥረዋል።
ልጁ እግሩ ነዳጅ መስጫው ላይ እንዲደርስለት የአሽከርካሪ ወንበሩ ጫፍ ላእ ተቀምጦ ያሽከረክር እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።
የአካባቢው አቃቤ ሕግቤተሰቡን ለመክሰስ እያሰቡ መሆናቸው ታውቋል።
ቤተሰቦቹ ሁለቱም ሥራ ነበሩ የተባለ ሲሆን መኪናውን አስነስቶ ሲሄድ ከወንድም እህቶቹ ጋር ቤት ትተውት መሄዳቸው ተገልጿል።
ፖሊስ የመኪና ቁልፍ ልጆች በማይደርሱበት ይቀመጥ ሲል አስጠንቅቋል።













