በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል የውይይት መድረክ ላይ ምን ተነሳ?

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ
ታትሟል

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል አጎራባች ቀበሌዎች በተፈጠሩ ግጭቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል። ግጭት ተፈጥሮ የነበረባቸው አካባቢዎች ወደ መረጋጋት መመለሳቸውን ተከትሎ፤ ቀላል የማይባሉ የሁለቱም ክልል ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት የተፈጠረውን ቁስል የማዳን እና የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር ኃላፊነት የእነሱ እንደሆነ ይናገራሉ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በግጭቶች ሳቢያ ተዘግተው የነበሩት መንገዶች መከፈታቸውን የሚያስረዱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ "ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ አድርገናል። በተለየ መልኩ ደግሞ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የነበረው የንግድ እንቅስቃሴዎች ወደ ቀድሞ ሁኔታዎች ተመልሰዋል" ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራው በፍላጎት ላይ የተመሰረት መሆኑን አስምረው ይናገራሉ። "ተፋናቃዮችን እንዲመለሱ ያደረግናቸው በሙሉ ፍላጎታቸው ላይ በመመስረት ነው። ማንም ያለ ፍላጎቱ እንዲመለስ አልተደረገም፤ ነገር ግን ለመመለስ ያልፈለጉ አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ወደ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው የሚሉት ምክትል ፕሬዝደንቱ፤ "ምርጥ ዘር እያቀረብን ነው። ከብድር አገልግሎት በተጨማሪ አስፈላጊ ፍላጎቶችን እያሟላን ነው" በማለት እነዚህ ድጋፎች ወደ ሁለቱም ክልሎች ለተመለሱ ተፈናቃዮች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

ምንም እንኳ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ቢመለሱም ከዚህ ቀደም ወደነበራቸው የኑሮ ዘይቤ መመለሱ ግን ጠንከር ያለን ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።

የድንበር ይገባኛል ግጭቶች

በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ለሚከሰቱ ግጭቶች እንደ ምክንያትነት ተደርገው ሲቀርቡ ከነበሩት መካከል የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አንዱ እንደሆነ ይነገራል።

ከድንበር ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄዳል ተብሎ ነበር። ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ የኦሮሚያ ክልል ምን እየሠራ ነው የተባሉት ምክትል ፕሬዝደንቱ "ግጭቶችን ለመፍታት መፍትሄ የሚሆነው ህዝበ ውሳኔ ማካሄድ ወይም ድንበር ማካለል አይደለም። ከዚህ ቀደም ለተከሰቱ ችግሮች ምክንያቱ ድንበር አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድም በተመሳሳይ መልኩ ከዚህ ቀደም ለተከሰቱት ግጭቶች ምክንያቱ የድንበር ጉዳይ አለመሆኑን ተናግረው ነበር።

"በመጀመሪያ ደረጃ ባለፉት ዓመታት ለተከሰቱት ግጭቶች ምክንያቱ የግጦሽ መሬት ወይም የድንበር ጉዳዮች አልነበሩም። የመንግሥት መዋቅር ያለበት አሻጥር ነው ሕዝቡን ክፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተው እና ያፈናቀለው።" በማለት ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።

ምክትል ፕሬዝደንት ሽመልስ በተመሳሳይ መልኩ ለግጭቶቹ መቀስቀስ እንደ ምክንያትነት የሚያቀርቡት "የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚፍጨረጨሩ የፖለቲካ ደላሎች" ያሏቸውን ነው።

በመሆኑም በሶማሌ እና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል ለተከሰተው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ መስጠትና የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት ማጠናከር መሆኑን ያነሳሉ።

"ይህ ቢሆን አይደለም ለሁለቱ ክልሎች ለአፍሪቃ ቀንድም ይተርፋሉ" ብለዋል -አቶ ሽመልስ።

የሞያሌ ነገር

ኢትዮጵያን ከኬንያ የምታዋስነዋ ከተማ- ሞያሌ፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በተደጋጋሚ የይገባኛል እሰጥ አገባዎች አልፎ አልፎም ግጭቶችን አስተናግዳለች። በዚህም የተነሳ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል።

ለዚህ ችግር መፍትሄ ለማበጀት ምን እየተሰራ ነው በማለት ለሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት ጥያቄ በቀረበላቸው ወቅት "ቅድሚያ የምንሰጠው ለሰላም ነው . . . በአሁኑ ወቅት ግጭቶች የሉም። በሞያሌ ከተማ ዙሪያ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ኦሮሚያ እና ከፌደራል መንግሥት ጋር በመወያየት መፍትሄ እንሰጣለን እንጂ፤ በአሁን ላይ መፍትሄው ይህ ነው ብዬ ለመናገር ይከብደኛል" ብለው ነበር።

የኦሮሚያ አቻቸው አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ "በሶማሌ ክልል የአስተዳደር ሪፎርም ከተካሄደ ወዲህ በሞያሌ ከተማ ሰላም ሰፍኗል" ካሉ በኋላ አክለውም "ትኩረታችን በአካባቢው ያለው የንግድ እንቅስቃሴን ማስቀጠል ነው። የተቀረው ግን በጊዜ ሂደት መፍትሄ የሚያገኝ ይሆናል" በማለት ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል።

በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች መካከል ከፍተኛ የሆነ የንግድ ልውውጥ እንደሚደረግ ምክትል ፕሬዝደንት ሽመልስ ይናገራሉ።

ጫት፣ እህል እና የቁም ከብት ከኦሮሚያ ወደ ሶማሌ ክልል የሚላኩ ሲሆን፤ በተቃራኒው ሸቀጦች፣ ዘይት እና በፋብሪካ የተቀነባበሩ እንደ ፓስታ እና መኮሮኒ ያሉ የታሸጉ ምግቦች ከሶማሌ ወደ ኦሮሚያ ከሚገቡ ምርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ተከስቶ በነበረው ግጭት መንገዶች በመዘጋታቸው በሁለቱ ክልሎች መካከል የነበረው ንግድ እጅጉን ተቀዛቅዞ እንደነበረ የሚናገሩት ምክትል ፕሬዝደንቱ፤ የንግድ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ለማስቀጠል፤ ምርቶች የሚገቡበት እና የሚወጡባቸውን የንግድ መስመሮች ለይቶ የማዘጋጀት ሥራዎችን ጨምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴች እየተካሄዱ እንደሆነ ተናግረዋል።